በበጀት ዓመቱ በወንጀል ጉዳይ የተመዘበረን ከ398 ሚሊየን ብር በላይ የመንግሥት ሃብት ማስመለስ ተችሏል።

7

ባሕር ዳር: ሐምሌ 14/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ምክር ቤት የሕግ፣ ፍትሕ እና አሥተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የሚከታተላቸውን እና የሚደግፋቸውን ተቋማት የ2017 በጀት ዓመት የእቅድ አፈጻጸም እየገመገመ ነው። የአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ ኀላፊ ብርሃኑ ጎሽም በበጀት ዓመቱ የተከናወኑ የተቋሙን እቅድ አፈጻጸም ለቋሚ ኮሚቴው አቅርበዋል። ቢሮ ኀላፊው እንደገለጹት በበጀት ዓመቱ የተለያዩ የመደበኛ እና የሪፎርም ሥራዎች እቅዶችን በማቀድ ከፈጻሚ አካላት ጋር የጋራ በማድረግ ወደ ተግባር መገባቱን ጠቁመዋል።

በበጀት ዓመቱ ቢሮው የተቋሙን አገልግሎት አሰጣጥ በማሻሻል በክልሉ የሕግ የበላይነት እንዲከበር እና የመንግሥት እና የሕዝብን ጥቅም ማሥከበር የሚያስችሉ በርካታ ሥራዎች መሠራታቸውን ገልጸዋል።
ከ5 ሺህ 600 በላይ ለሚኾኑ የቀበሌ ማኅበራዊ ፍርድ ቤት ዳኞች ሥልጠና ተሰጥቷል ብለዋል። ከተለያዩ ተቋማት ጋር በመቀናጀት ባሕላዊ ፍርድ የሚሰጡ አካላትን የመለየት ሥራ መሠራቱንም አመላክተዋል።
በበጀት ዓመቱ በወንጀል ጉዳይ የተመዘበረን በጥሬ ገንዘብ ከ398 ሚሊዮን ብር በላይ የመንግሥት ሃብት ማስመለስ መቻሉን ገልጸዋል። ከ285 ሺህ ካሬ ሜትር በላይ የሚኾን የከተማ መሬት ማሥመለስ እንደተቻለም ነው ያብራሩት።
ከወንጀል ጋር በተያያዘ በገንዘብ ቅጣት 15 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር በላይ ለመንግሥት ገቢ ማድረግ እንደተቻለም ገልጸዋል።

የውዝፍ መዝገብን ከማጣራት በኩል የተሻለ ሥራ መሠራቱንም አንስተዋል። 44 የሚኾኑ ልዩ ልዩ ደንቦች እና መመሪያዎችን በማርቀቅ ለተለያዩ ተቋማት መስጠት እንደተቻለም አብራርተዋል።
የፍትሕ አሠራሩን ከአጋር እና ባለድርሻ አካላት ጋር ተቀናጅቶ ለመሥራት የሚያስችል መግባቢያ ሰነድ በመፈራረም መሥራት እንደተቻለም አንስተዋል።
ከስድስት በላይ ማሥተባበሪያ ጽሕፈት ቤቶችንም በመክፈት የፍትሕ ተደራሽነትን ለማስፈን ጥረት ተደርጓል ነው ያሉት። ጠበቆች የፍትሕ አጋዥ እንዲኾኑ በየደረጃው ሰፊ ውይይቶች መደረጉንም ነው ያመላከቱት።

በሴቶች እና ሕፃናት ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎች ተገቢውን ፍትሕ እንዲያገኙ ለብቻው ተይዞ እየተሠራ ስለመኾኑም አንስተዋል። ያለ እድሜ ጋብቻን ለማስቀረት ሥልጠና መሥጠትን ጨምሮ ሰፊ ሥራ መሠራቱን ጠቁመዋል።
ከ247 ሺህ በላይ የውል እና ማስረጃ ሰነዶችን በመመዝገብ እና በማረጋገጥ 681 ሚሊዮን ብር በላይ ገንዘብ ለመንግሥት ገቢ ማድረግ መቻሉን አብራርተዋል።
አቅም ለሌላቸው እና በነጻ ሕግ ድጋፍ ለተደረገላቸው ዜጎች ተከራክሮ በማስፈረድ በ574 መዝገቦች ከ41 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ እንዲፈጸምላቸው መደረጉን አብራርተዋል።
የዲጂታል ሥርዓትን በመጠቀም ከክልል እስከ ወረዳ ድረስ በዘመናዊ መንገድ የመረጃ ልውውጥ እየተደረገ ስለመኾኑም አንስተዋል። ተቋሙ የተመደበለትን በጀት በአግባቡ መጠቀሙን አንስተዋል።

ዘጋቢ፦ አሰፋ ልጥገበው

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበባሕር ዳር ከተማ ውስጥ 12 ሺህ ነጋዴዎች ሕጋዊ ኾነው እንዲሠሩ ተደርጓል።
Next articleበምሥራቅ ጎጃም ዞን ከ25 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለማግኘት እየተሠራ ነው።