በባሕር ዳር ከተማ ውስጥ 12 ሺህ ነጋዴዎች ሕጋዊ ኾነው እንዲሠሩ ተደርጓል።

10

ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 14/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳድር ሕገ ወጥ ንግድን በቅንጅት በመከላከሉ አዎንታዊ ለውጥ መምጣቱን አሚኮ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች እና መንግሥታዊ ተቋማት ገልጸዋል።

ወይዘሮ ጥላነሽ አብርሃም የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪ ናቸው። እሳቸው እንደሚሉት በምሽት ከጎዳና ላይ ቸርቻሪዎች ከአንድም ሁለት ጊዜ የገዙት ሙዝ የወይበ መኾኑን አንስተዋል። በተጨማሪም “ሁለት ኪሎ ግራም ነው” ተብለው የወሰዱት ሙዝ በቤታቸው ሲመዝኑት 500 ግራም ቀንሶ እንዳገኙት ጠቁመዋል።

ከጎዳና ላይ ቸርቻሪዎች የምፈልገውን በቅርበት ማግኘቱ ጥሩ ቢኾንም በተለይ በምሸት የሚደረግ ግብይት ወከባው ስለሚያበዛ ስርቆት ያየለበት ነው ብለዋል።

በጎዳና ላይ ተቀምጠውም ኾነ በካሬታ እየተንቀሳቀሱ የሚሸጡ ቸርቻሪዎች ለገበያ ከሚያቀርቡት ፍራፍሬ ላይ ጥሩውን ከላይ እያሳዩ ከውስጥ የተበላሸውን ደብቀው ይሸጣሉ ነው ያሉት። ተገልጋዩንም የዋጋውን ቅናሽ በማየት ብቻ ጥራት የሌለውን ሸቀጥ ሲገዛ መታዘባቸውን ተናግረዋል።

አስተያዬት ሰጪያችን አያይዘውም በቅርቡ የከተማው ደንብ አስከባሪዎች የጎዳና ላይ ቸርቻሪዎችን በመቆጣጠራቸው ገበያተኛው ከሕጋዊ ነጋዴዎች እንዲገበያይ አድርጎታል ብለዋል።

ሌላው ወጣት ሱራፌል ብርሃኑ የጎዳና ላይ ቸርቻሪዎች ቋሚ የመሸጫ ቦታ ስለለላቸው እየተዘዋወሩ በመሸጥ ያጭበረብራሉ ነው ያለው። ለአብነትም “በርከት ያለ ዕንቁላል የገዛሁት ባለ ካሬታ ቸርቻሪ ተመልሸ ስመጣ ስራውን አውቆ ከአካባቢው ተሰውሯል” በማለት ገልጿል። በመኾኑም መንግሥት ተዘዋዋሪዎችንም ኾነ የጉልት ቸርቻሪዎችን ሕጋዊ መስመር ማስያዝ አለበት ነው ያለው።

የባሕር ዳር ከተማ አስተዳድር ንግድ እና ገበያ ልማት መምሪያ ኀላፊ አደራ ጋሼ በከተማዋ በሕገ ወጥ መንገድ ጎዳና እየዘጉ የሚነግዱ ግለሰቦችን ወደ ሕጋዊ መስመር ለማስገባት “የገበያ አረጋጊ እና ጸረ ኮንትሮባንድ” ግብረ ኃይል በማቋቋም በቅንጅት እየሠሩ እንደሚገኙ አስታውቀዋል።

ግብረ ኃይሉ ሕገ ወጥ ንግድን እየተከላከለ በመምከር ወደ ሕጋዊ መስመር እንዲገቡ እያደረገ ነው ብለዋል።

ከዚህ በፊት በባሕር ዳር ከተማ የጎዳና ላይ ንግድ ከመስፋፋቱ አኳያ ትራፊኩን አደናቅፎ ነበር ያሉት መምሪያ ኀላፊው ሕገ ወጡ በርትቶም ሕጋዊ ነጋዴው ከገበያ እንዲወጣ አድርጎ ነበር። ይህን በመገንዘብ መምሪያው ከጸጥታ ኃይሉ ጋር ተናቦ በመሥራቱ 11ሺህ 947 አዳዲስ ነጋዴዎች ወደ ሕጋዊ መስመር እንዲገቡ አድርጓል ብለዋል።

የባሕር ዳር ከተማ አስተዳድር የደንብ ማስከበር አገልግሎት መምሪያ ኀላፊ ኃይለሚካኤል አርዓያ ቀደም ሲል በከተማዋ ሕጋዊው እና ሕገወጥ ነጋዴዎች የማይለዩበት የተተረማመሰ ንግድ ይደረግ እንደነበር አስታውሰዋል። ይሁንና ከተማ አስተዳድሩ በቅንጅት በመሥራቱ ሕገ ወጥ ንግድን መከላከል ተችሏል ብለዋል።

በበጀት ዓመቱም ሕግን ተላልፈው የተገኙ ነጋዴዎችን በመቅጣት ከ, ሚሊዮን በላይ ብር ገቢ ተደርጓል። ቅጣቱም በርካታ ሕገ ወጥ ነጋዴዎች ወደ ሕጋዊ መረብ እንዲመጡ አድርጓቸዋል ነው ያሉት።

ሕገ ወጥ ንግድን መቆጣጠር በመቻሉ ኀብረተሰቡ ምስጋናውን ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ እየገለጸ እንደሚገኝም አቶ ኃይለሚካኤል ተናግረዋል።

ይህ የቁጥጥር እና ሕግ የማስከበር ሥራ ዘላቂ እንዲኾን ኀብረተሰቡ የእስካሁኑን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል አቶ ኃይለሚካኤል ጥሪ አቅርበዋል።

ዘጋቢ፦ ሙሉጌታ ሙጨ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleዘላቂ ሰላምን ለማምጣት የተሰበሩ እሴቶችን መጠገን ላይ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት ይገባል።
Next articleበበጀት ዓመቱ በወንጀል ጉዳይ የተመዘበረን ከ398 ሚሊየን ብር በላይ የመንግሥት ሃብት ማስመለስ ተችሏል።