ዘላቂ ሰላምን ለማምጣት የተሰበሩ እሴቶችን መጠገን ላይ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት ይገባል።

8

ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 14/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የዓለም የሰላም መረጃ ጠቋሚ (ጂፒአይ) በፈረንጆቹ አቆጣጠር በ2024 ያወጣው መረጃ እንደሚያሳየው አይስላንድ፣ ዴንማርክ፣ አየርላንድ፣ ኒውዚላንድ እና ሲንጋፖር በዓለም ላይ ሰላም የሰፈነባቸው ሀገራት ኾነው ተቀምጠዋል።

ለዚህ ደግሞ ጠንካራ አሥተዳደር እና የሕግ የበላይነት፣ ገለልተኛ የጸጥታ ተቋማት መኖር፣ ሕግን በፍትሐዊነት ማስከበር መቻላቸው፣ ባሕላዊ እሴቶች፣ አካታች እና ማኅበራዊ ፍትሕ ማስፈን መቻላቸው እንደ ምክንያት ተቀምጠዋል።

ማረሚያ ቤቶቻቸው ታራሚዎችን ባለምግባር ሰው አድርገው የሚያወጡ መኾኑ፣ የተረጋጋ ኢኮኖሚ ያላቸው፣ ግጭትን የሚከላከሉ እና ሥምምነትን የሚያበረታቱ ፖሊሲዎችን ማጣመራቸው ለሰላማዊነተታቸው ተጨማሪ መንገዶች ናቸው።

በሌላ በኩል በርካቶቹ የአፍሪካ ሀገራት በጦርነት እና ግጭት አዙሪት ውስጥ ከሚገኙ ሀገራት በቀዳሚነት ተቀምጠዋል። በኢትዮጵያ የሰላም መደፍረስ ምክንያቶች ምን ሊኾኑ ይችላል?

የአማራ ክልል በጦርነት የተጎዱ አካባቢዎች መልሶ ማቋቋም እና ግንባታ ፈንድ ጽሕፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር አባተ ጌታሁን (ዶ.ር) በኢትዮጵያ ለተከሰተው የሰላም መሸርሸር ምክንያቶችን አስቀምጠዋል።

የታሪክ እና የኅብረ ብሔራዊነት አረዳድ እና አተረጓጎም በኢትዮጵያውያን የተቀመረ ሳይኾን ከውጭ የመጣ መኾኑ የፖለቲካ ሂደቱ ዋልታ ረገጥ እንዲኾን አድርጎታል ብለዋል። የባሕል እና ሃይማኖቶች መዳከምም ሌላኛው ችግር እንደኾነ አስቀምጠዋል።

ዘመናዊ ትምህርቱ ባሕላዊ እሴቶችን ያገለለ፣ የምዕራባውያን ዕውቀት ላይ ብቻ ያተኮረ መኾኑንም ገልጸዋል። የመገናኛ ብዙሃን በሥነ ምግባር እና በሙያ የተቃኙ ከመኾን ይልቅ ዋልታ ረገጥ አሥተሳሰብ ላይ መቆምም ሌላኛው ችግር ነው።

በቀጣናው የቆየው ታሪካዊ ዳፋ ሌላኛው ፈተና ነው። ቅኝ ገዥዎች በቅኝ ግዛት ዘመን በጎረቤት ሀገራት ላይ ጥለውት ያለፉት ሳንካ አሁንም ድረስ ችግር ኾኖ ቀጥሏል።

ኢትዮጵያን በወረሩበት ወቅትም በኢትዮጵያውያን መካከል የተጠቀሙበት የክፍፍል ሴራ ባለፉት ዓመታት መዋቅራዊ ኾኖ በመቀጠሉ ሀገሪቱን ችግር ላይ እንድትወድቅ አድርጓታል ብለዋል።

ኢትዮጵያ ካላት ጠንካራ ታሪክ፣ የተፈጥሮ ሃብት እና ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥር አኳያ “በቀጣናው የበላይነትን ትቀዳጃለች” በሚል ስጋት የግጭት ምቹ ሁኔታዎችን በመጠቀም በማበጣበጥ የማዳከም ሥራ እየሠሩ መኾኑን ገልጸዋል።

ቀጣናው የአውሮፓ፣ የእስያ እና የአፍሪካ ኮሪደር እና የጂኦ ፖሊቲካ መቀመሪያ፣ የሀያላን ሀገራት መናኽሪያ፣ የሽብርተኝነት እና አከራሪነት እምብርት መኾኑ ሌላኛው ፈተና መኾኑን ገልጸዋል። በሀገራት መካከል ግልጽ የኾነ ድንበር እና ወሰን አለመኖር በቀጣናው የተዳፈነ እሳት ወይንም ጊዜውን ጠብቆ የሚፈነዳ ችግር እንዲኾን አድርጎታል። የወጣቶች ሥራ አጥነት እና የሥነ ምግባር ጉድለቶች ማኅበራዊ ቀውሶች መስፋፋት ለሰላሙ መደፍረስ ምክንያቶች መኾናቸውንም አብራርተዋል።

ዋና ዳይሬክተሩ እንዳሉት በሀገሪቱ ብሎም በአማራ ክልል በተፈጠረው የጸጥታ ችግር ከፍተኛ ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ጉዳት ደርሷል። ፈንድ ጽሕፈት ቤቱ ከምሁራን እና ባለድርሻ አካላት ጋር በመኾን በሰሜኑ ጦርነት እና አሁን ላይ በክልሉ በተፈጠረው ግጭት የደረሰውን ሰብዓዊ፣ ቁሳዊ እና የሥነ ልቦና ጉዳት ጥናት ማድረጉን ገልጸዋል። በጥናቱ የግጭቱ ዋና ምክንያቶች፣ የግጭቱ ተዋናይች እና ግጭቱን በአጭር፣ በመካከለኛ እና በረጅም ጊዜ ለመፍታት የሚያስችሉ መፍትሄዎች ተቀምጠዋል ብለዋል።

የቀጣናውን ነባራዊ ሁኔታ ታሳቢ ያደረገ የአምስት ዓመት ስትራቴጅ እቅድ መታቀዱን ገልጸዋል። የስትራቴጅክ ዕቅዱ በክልሉ ጠንካራ የጸጥታ ተቋማትን በመገንባት፤ የሕግ የበላይነት ማረጋገጥ፣ ዘላቂነት ያለው አስተማማኝ ሰላም በማስፈን በክልሉ ለሚከናወኑ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊ እና ፖሊቲካዊ ተግባራት ምቹ የጸጥታ ሁኔታ ለመፍጠር ያለመ ነው።

ተቋም እና አመራር ግንባታ፣ የሕግ የበላይነት እና ሁለንተናዊ ዘላቂ ሰላም ግንባታ፣ የድኅረ ግጭት አሥተዳደር ግንባታ እና የቀድሞ ተዋጊዎችን ወደ ሰላማዊ ሕይዎት መመለስ የስትራቴጅክ እቅዱ ዋና ዋና ተግባራት ኾነው ተቀምጠዋል። ብዝኀነትን ማሥተዳደር፣ ሚዲያ እና የሕዝብ ግንኙነት ሥራን ማሻሻል፣ የመልካም አሥተዳደር ግንባታ፣ መልካም ግንኙነት፣ የባሕል እና ሰላም እሴት ግንባታዎ ሌሎች የስትራቴጅክ እቅዱ የትኩረት መሥኮች መኾናቸውን ነው የገለጹት። ክልሉን ወደ ተሟላ ሰላም ለመመለስ እውነተኛ ውይይቶችን ማካሄድ ያስፈልጋል ብለዋል። መንግሥት፣ ማኅበረሰቡ እና ምሑራን በተናበበ መንገድ ሊሠሩ ይገባል ብለዋል።

የአማራ ክልል ሥራ አመራር ኢንስቲትዩት ምክትል ፕሬዝዳንት ቹቹ አለባቸው (ዶ.ር ) እንዳሉት ለአማራ ክልል ግጭት መሠረታዊ ምክንያቶች ከታሪክ እና ትርክት ጋር የተያያዘ ቢኾንም መልካም አሥተዳደር፣ የመልማት ጥያቄ፣ ሥራ አጥነት እና ሌሎች ችግሮች የግጭቱ አባባሽ ምክንያቶች ናቸው።

ግጭትን ለማስቆም በአጭር፣ በመካከለኛ እና በረጅም ጊዜ ለይቶ መፍታት እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል። ግጭቱን ማስቆም የአጭር ጊዜ መፍትሄ መኾኑን ያነሱት ዶክተር ቹቹ ለዚህ ደግሞ በእውነተኛ ድርድር በአጭር ጊዜ ችግሩን በመፍታት በተራዘመ ግጭት ሊደርስ የሚችለውን ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ውድመት ማስቆም ይገባል ብለዋል።

ከችግሩ ለመውጣት በቀጣይ መንግሥት ሥራ አጥነትን መቀነስ፣ ፍትሐዊ የልማት ተደራሽነት ማስፋት እና የተሰበሩ እሴቶችን መጠገን ላይ ትኩረት ሰጥቶ ሊሠራ ይገባል ብለዋል። ከመንግሥት ባለፈ የሃይማኖት ተቋማት እና ሲቪክ ማኅበራት ትልቁ ድርሻ ወስደው ሊሠሩ ይገባል ብለዋል።

ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleከ1ሚሊዮን በላይ ለሚኾኑ ዜጎች የሥራ ዕድል ተፈጥሯል።
Next articleበባሕር ዳር ከተማ ውስጥ 12 ሺህ ነጋዴዎች ሕጋዊ ኾነው እንዲሠሩ ተደርጓል።