
ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 14/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል የሥራ አጥ ቁጥርን ለመቀነስ ከመቸውም ጊዜ በላይ እየተሠራ ይገኛል። በዚህ ሂደት ውስጥም በርካቶች ለሥራ በቅተዋል።
የሥራ ዕድሎች ከጎበኟቸው ወጣቶች መካከል ወጣት አሸናፊ ሞላ እና ወጣት ሞላ ተስፋው ይገኙበታል።
ወጣት አሸናፊ በ2015 ዓ.ም ከተመረቀ በኋላ ሥራ በማጣት ከቤተሰቡ ጋር ይኖር ነበር።
ይኹን እንጂ በደብረማርቆስ ከተማ የጎዛምን ወረዳ ሥራ እና ሥልጠና ጽሕፈት ቤት ባመቻቸው ሥልጠና እና ከጓደኞቹ ጋር በመደራጀት በውኃ እና ኢነርጂ ጽሕፈት ቤት ስር በመሥራት የገጠር ማኅበረሰቡን የንጹህ መጠጥ ውኃ ተደራሽነትን የማረጋገጥ ሥራ እየሠራ ይገኛል።
በተጨማሪም የቧንቧ ውኃ ጥገና መለዋወጫዎችን በተመጣጣኝ ዋጋ በማቅረብ፣ ፈሳሽ ሳሙና በማምረት እና በመሸጥ የውስጥ ገቢያቸውን ለማሳደግ እየሠሩ ነው።
“ሥራውን የጀመርንበት ጊዜ ቅርብ ከመኾኑ ጋር ተያይዞ ይህን ያክል ለውጥ አምጥተናል ማለት ባይቻልም እንደጅምሩ እና እንቅስቃሴው የተሻለ ደረጃ ያደርሰናል የሚል ተስፋ አለኝ” ሲል ወጣት አሸናፊ ይናገራል።
ወጣት ሞላ ደግሞ የጎዛምን ወረዳ ነዋሪ ሲኾን በ2013 ዓ.ም ከዩኒቨርሲቲ ተመርቆ ሥራ አጥቶ ከቤተሰቡ ጋር ይኖር ነበር።
የወረዳው ሥራ እና ሥልጠና ጽሕፈት ቤት ለሥራ ፈላጊ ወጣቶች ባወጣው ማስታወቂያ መሠረት ዕድሉን አግኝቶ በመሠልጠን እና በማኅበር በመደራጀት የሕንጻ ሥራ ተቋራጭ ፈቃድ በማውጣት የማኅበረሰብ መድኃኒት ቤት ግንባታ ሥራ ላይ ተሰማርቷል።
ከዚህ ሥራ ጥሩ ተጠቃሚ መኾኑን የገለጸው ወጣት ሞላ በቀጣይ ማኅበራቸውን ወደ አክሲዮን በማሳደግ የተሻለ ገቢ ለማግኘት ጥረት እያደረጉ መኾኑን አስረድቷል።
የአማራ ክልል ሥራ እና ሥልጠና ቢሮ በክልሉ ያለውን የሥራ አጥነት ችግር ለመቅረፍ ባደረገው ጥረት ከ1 ነጥብ 3 ሚሊዮን በላይ ለሚኾኑ ዜጎች ቋሚ እና ጊዜያዊ የሥራ ዕድል መፍጠር መቻሉን ይገልጻል።
የተፈጠሩት የሥራ ዕድሎች ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ለሚገኙ ዜጎች ተስፋን የሰጡ ስለመኾናቸውም ነው የሚነገረው።
ይህ ስኬት ከታቀደው በላይ መኾኑን የአማራ ክልል የሥራ እና ሥልጠና ቢሮ የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊ አንዳርጋቸው ጎፋ ለአሚኮ አብራርተዋል።
የቢሮው መረጃ እንደሚያመለክተው በ2017 በጀት ዓመት ለ1 ሚሊዮን 233 ሺህ 744 ዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ታቅዶ ነበር።
በተለያዩ የሙያ ዘርፎች ሥልጠና እና የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች ከተሠሩ በኋላ ለ1ሚሊዮን 313 ሺህ 986 ዜጎች ቋሚ እና ጊዜያዊ የሥራ ዕድል ተፈጥሯል ነው ያሉት።
ይህ አፈጻጸም ከእቅዱ በላይ ሲኾን በአኹኑ ወቅት ባለው አንጻራዊ ሰላም እና መንግሥት በዘረጋው የተለያዩ የፕሮጀክት ሥራዎች ምክንያት መሳካቱ ተመላክቷል።
በሥራ ዕድሉ ተጠቃሚ ከኾኑት መካከል 43 ነጥብ 42 በመቶ የሚኾኑት ሴቶች መኾናቸውንም ጠቅሰዋል።
ቢሮው የሥራ ዕድል ከመፍጠር ባሻገር በርካታ የድጋፍ ሥራዎችን እንዳከናወነም ተገልጿል።
የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊው ይህንን ሥራ ለመሥራት አልጋ በአልጋ እንዳልነበር ገልጸዋል።
ባለው የጸጥታ ችግር ምክንያት በርካታ ኮሌጆች ወደ ሥልጠና አለመግባታቸው የሥራ ፈላጊ ዜጎችን ከማሠልጠን አንፃር ውስንነት እንደፈጠረ አስረድተዋል።
በተጨማሪም አዳዲስ ኢንተርፕራይዞች ወደ ሥራ ሲገቡ የሥራ ልምድ ያስፈልጋቸዋል የሚለው መመሪያ እና አዲስ የንግድ ፈቃድ ለማውጣት ዲጂታል በመኾኑ ከኔትወርክ ችግር ጋር ተያይዞ የነበረው ውሱንነት ከገጠሟቸው ተግዳሮቶች መካከል ተጠቃሽ እንደኾኑም ጠቅሰዋል።
ቢሮው ለቀጣይ የገጠሙትን ተግዳሮቶች በመቅረፍ ለ2018 በጀት ዓመት “የቁጭት ዕቅድ” በማቀድ የተሻለ ሥራ ለመሥራት የንቅናቄ ሥራ እየሠራ መኾኑንም አብራርተዋል።
የተሠራው ሥራ ግን የአማራ ክልል መንግሥት የሥራ አጥነትን ችግርን ለመቅረፍ እና የዜጎችን ኑሮ ለማሻሻል የሚያደርገውን ቁርጠኝነት የሚያሳይ ታላቅ ስኬት እንደኾነም ነው የጠቆሙት።
በቀጣይም ተጨማሪ የሥራ ዕድሎች እንዲፈጠሩ እና ዘላቂ መፍትሄ እንዲገኝ ቢሮው የሚያደርገው ጥረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አብራርተዋል።
ዘጋቢ፦ ሰናይት በየነ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን