
አዲስ አበባ:ሐምሌ 14/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ላለፉት ስድሰት ዓመታት ሥራ ላይ ያዋለውን የኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ እና የምርጫ ሥነ ምግባር አዋጅ 1162/2011ን መሻሻሉን አስታውቋል።
ቦርዱ የአዋጁን ማሻሻያ አስመልክቶ ለመገናኛ ብዙኃን ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል።
መግለጫውን የሰጡት የቦርዱ ዋና ሠብሣቢ ሜላትወርቅ ኀይሉ ቦርዱ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ሰፊ ውይይት እና ምክክር ሲያደርግ ከቆየ በኋላ 26 የአዋጅ ድንጋጌዎች ላይ ማሻሻያ ማድረጉን አስታውቀዋል።
የማሻሻያ አዋጁ ሐምሌ 10/2017 ዓ.ም ማጽደቁንም ገልጸዋል።
በሀገሪቱ ከ50 ሺህ በላይ የምርጭ ክልል ጣቢያዎች መኖራቸውን የገለጹት ዋና ሠብሣቢዋ የምርጫ ክልል ኀላፊዎች እንደ ምርጫ ክልል ጣቢያዎች ብዛት እንዲወሰን መጽደቁን ተናግረዋል።
የምርጫ ጣቢያው ኀላፊ በምርጫ ሂደት የሚመጡ ቅሬታዎችን በሕግ በተሰጠው ሥልጣን መሠረት ፈጣን እና ግልጽ የቅሬታ ውሳኔዎችን መስጠት ይችላል።
ስለ ምርጫ ሕግ እና አፈጻጸም የበቁ አስፈጻሚዎች በሁሉም የምርጫ ክልሎች እንደሚመደቡም አንስተዋል።
የአንድ ሰው የመራጭ ዕድሜ በምዝገባ ጊዜ ሳይኾን በምርጫ ጊዜ እንዲኾን ተሻሽሎ መቅረቡንም አንስተዋል።
ከአሁን በፊት የመራጭ ዕድሜ በምዝገባ ጊዜ 18 ዓመት ካልሞላው መምረጥ አይችልም ነበር። አሁን ግን በተሻሻለው አዋጅ መሠረት መራጩ በምርጫ ጊዜ 18 ዓመት ከሞላው የመምረጥ ዕድል እንዳለው ተደንግጓል ነው ያሉት።
ከሕዝብ ተወካዮች እና ከክልል ምክርቤት ተወካዮች በተጨማሪ የሴቶችን እና አካል ጉዳተኞችን ተሳትፎ ለማበረታታት የሚያስችል የእጩዎች የድጋፍ ፊርማ መሻሻሉንም አንስተዋል።
ሴቶች እና አካል ጉዳተኞች በመገናኛ ብዙኃን ተሳትፏቸውን መግለጽ የሚችሉበት አሠራር መሻሻሉንም ተናግረዋል።
አንድ ፓርቲ ሀገራዊ ፓርቲ ኾኖ ለመቋቋም በሚኖርበት ክልል ከ40 በመቶ የማይበልጥ መደበኛ ነዋሪዎች በአባልነት ሊኖሩት እንደሚገባ በአዋጁ ተሻሽሎ መቅረቡንም ገልጸዋል።
ሀገራዊ ፓርቲ ነኝ የሚል ፓርቲ በሀገሪቱ ባሉ ክልሎች 50 በመቶ የሚኾኑ አካባቢዎች ላይ ተሳታፊዎች ሊኖሩት ይገባል።
ማንኛውም የፖለቲካ ፓርቲ በመንግሥትም ኾነ በግል ተቋማት የሚሠሩ የፖለቲካ ፓርቲ አባላት ላይ ያለፈቃዳቸው ከደሞዛቸው ላይ ገንዘብ መቁረጥ እንደማይችል ምርጫ ቦርድ ገልጿል።
በ7ኛው ሀገራዊ ምርጫ በተወሰኑ የምርጫ አካባቢዎች የመራጮች እና የእጩዎች ምዝገባ በቴክኖሎጅ በታገዘ መልኩ ለማስኬድ የተጀመሩ ሥራዎች መጠናቀቃቸውንም አንስተዋል።
የፖለቲካ ፓርቲም ኾነ የግል ዕጩዎች ሞዝገባ ላይ የብሔራዊ መታወቂያ መኖር ግዴታ እንደኾነም ተጠቁሟል።
ዘጋቢ፡- ቴዎድሮስ ደሴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!