የመስኖ ፕሮጀክቶችን በተያዘላቸው ጊዜ ማጠናቀቅ መቻሉን የኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር አስታወቀ።

9

ከሚሴ: ሐምሌ 14/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር በ2017 በጀት ዓመት ተገንብተው የተጠናቀቁ የመስኖ መሠረተ ልማት ሥራዎች ለአገልግሎት ክፍት ኾኑ።

በብሔረሰብ አሥተዳደሩ የጅሌ ጥሙጋ እና የአርጡማ ፉርሲ ወረዳ አርሶ አደሮች ተገንብተው ለአገልግሎት ክፍት በኾኑላቸው የመስኖ ፕሮጀክቶች መደሰታቸውን ገልጸው ተገቢውን ጥበቃ ለፕሮጀክቶቹ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል።

ፕሮጀክቶቹ የአርሶ አደሮቹ የረጅም ጊዜ የመልካም አሥተዳደር ጥያቄዎች እንደነበሩ ጠቅሰው አሁን ላይ በዓመት ሦሥት ጊዜ ለማምረት እንደሚሠሩም ገልጸዋል።

የኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር መስኖ እና ቆላማ አካባቢዎች መምሪያ ኀላፊ አሕመድ ጅብሪል በ2017 በጀት ዓመት በክልሉ በዘላቂ ልማት በጀት፣ በሴፍቲኔት ካፒታል እና በወረዳዎች በጀት በአጠቃላይ ከ437 ሚሊዮን ብር በላይ በኾነ ወጭ 23 የመስኖ ፕሮጀክቶችን በመገንባት ለአገልግሎት ክፍት ተደርጓል ነው ያሉት።

የመስኖ መሠረተ ልማት ሥራዎቹ በሚገነቡበት ወቅት የማኅበረሰቡ ተሳትፎ የላቀ እንደነበር ገልጸው በዚህም ከ1 ሺህ 600 በላይ አርሶ አደሮች ፕሮጀክቶቹን በጉልበት በመደገፍ ከ4 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ወጭን ማዳን መቻሉን አስረድተዋል።

የተገነቡት 23 የመስኖ ፕሮጀክቶች ከ3 ሺህ 271 በላይ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ መኾኑንም ኀላፊው ገልጸዋል።

የመስኖ ፕሮጀክቶቹ በዘላቂነት እንዲጠበቁም የመስኖ ማኅበራትን በማቋቋም እና ሥልጠና በመስጠት ወደ ሥራ እንዲገቡም መደረጉን አስገንዝበዋል።

በ2018 በጀት ዓመትም ከ12 በላይ የመስኖ አውታሮችን በብሔረሰብ አሥተዳደሩ ለመገንባት መታቀዱንም ከመምሪያው ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

ዘጋቢ:- ይማም ኢብራሒም

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የአንድነታችን አርማ የኅብረታችን ካስማ በኾነው ባሕር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲዬም አረንጓዴ አሻራችንን አስቀምጠናል” ሙሉነሽ ደሴ (ዶ.ር)
Next articleየኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ እና የምርጫ ሥነ ምግባር አዋጅ 26 የአዋጅ ድንጋጌዎች ላይ ማሻሻያ አድርጓል።