
ደብረ ብርሃን:ሐምሌ 14/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በደብረ ብርሃን ዩንቨርሲቲ የባሕላዊ የሕክምና መድኃኒቶች ላይ ያተኮረ ምክክር እየተካሄደ ነው። የምክክር መድረኩን ያዘጋጀው የአማራ ክልል የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ነው።
የደብረ ብርሃን ዩንቨርሲቲ የምርምር እና ቴክኖሎጂ ሽግግር ምክትል ፕሬዝዳንት ሲሳይ ሙላቴ (ዶ.ር) ባሕላዊ የሕክምና መድኃኒቶችን ከዘመናዊ ሕክምና ጋር ለማስተሳሰር የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ኀላፊነት አለባቸው ብለዋል። በባሕላዊ ሕክምና እና ሀገር በቀል ዕውቀት ላይ ገና እንዳልተሠራም ተናግረዋል።
በዚህ ዘርፍ የደብረ ብርሃን ዩንቨርሲቲ በ10 ምርምሮች ውጤታማ እየኾነ መምጣቱን ገልጸዋል። ከእነዚህም ውስጥ ሦስት ምርምሮች ተጠናቅቀዋል ነው ያሉት።
የአማራ ክልል ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር በላይ በዛብህ ባሕላዊ መድኃኒት የክልሉ አንዱ ሀብት ነው ብለዋል።
የክልሉ ሀብት የኾነውን ዘርፍ ለማሳደግም መድኃኒት የኾኑ እፅዋትን መሰብሰብ ያስፈልጋል ብለዋል። ይህንን ለመተግበር የዘርፉ ባለሙያዎችን ከዘመናዊ ዕውቀት ጋር በማስተሳሰር ውጤታማ ሥራ መሠራት እንደሚገባ አመላክተዋል።
በመድረኩ ላይ በዘርፉ የዩኒቨርሲቲው ተመራማሪዎች እና የአማራ ክልል ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል።
ዘጋቢ:- ወንዲፍራ ዘውዴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!