
ጎንደር: ሐምሌ 14/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የሰላም ሚኒስቴር “ማኅበራዊ ትስስራችን ለአብሮነታችን” በሚል መሪ መልዕክት የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የቃል ኪዳን ቤተሰብ ሀገር አቀፍ የልምድ ልውውጥ መድረክ በጎንደር ዩኒቨርሲቲ አካሂዷል።
በመርሐ ግብሩም የፌደራል፣ የክልል እና የዩኒቨርሲቲው የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል። ውይይቱ የጎንደር ዩኒቨርሲቲን የቃል ኪዳን ቤተሰብ ተሞክሮን ወደ ሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች ለማስፋት ያለመ ነው።
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት አሥራት አጸደወይን (ዶ.ር) ለመቀራረብ እና አብሮ ለመኖር የሚያስችሉንን እሴቶች አስቀጥሎ መዝለቅ ለሀገር ጠቃሚ ነው ብለዋል።
ዛሬም ድረስ እንግዳ በመቀበል ጎንደር ለሀገር አንድነት እየሠራች እንደምትገኝም አንስተዋል። የጎንደር ዩኒቨርሲቲ እንዲመሠረት የጎንደር ሕዝብ ሃብቱን፣ ጉልበቱን እና አቅሙን ሳይሰስት መስጠቱንም አስታውሰዋል።
የጎንደር ሕዝብ የዩኒቨርሲቲውን ራዕይ ለማሳካት ከሌላ ቦታ እና ብሔር የሚመጡ ልጆችን በቃል ኪዳን በመቀበል እንደ ልጁ እያየ እያስተማረ መኾኑን ተናግረዋል።
የመተሳሰብ ተምሳሌት የኾነውን የቃል ኪዳን ቤተሰብ በጎ ተግባር የአካባቢውን እንግዳ ተቀባይነት፣ አብሮነት እና የአንድነት መስተጋብርን የሚያሳይ መኾኑን አንስተው ሀገራዊ አንድነትን ለማጠናከር ያለመ በመኾኑ ኅብረተሰቡ ጠብቆ እየሠራበት መኾኑንም አስታውቀዋል።
በሀገራችን የሚገኙ እሴቶችን መጠበቅ እና አብሮነትን ማስቀጠል ላይ መሥራት ጥሩ ውጤት እንደሚያስገኝ ከጎንደር የቃል ኪዳን ቤተሰብ መማር እንደሚቻልም ዶክተር አስራት ተናግረዋል።
የጎንደር ዩኒቨርስቲ የቃል ኪዳን ተግባርን በሁሉም ተቋማት ማስተግበር አንድነትን እና አብሮነትን ለማሳደግ ትልቅ ድርሻ የሚወስድ በመኾኑ ልምድ ልውውጡን ለማጠናከር ሊሠራ ይገባል ብለዋል።
የሰላም ሚኒስትር ሙሐመድ እድሪስ ከጎንደር አብሮነትን እና ፍቅርን ተምረናል ብለዋል። የተጀመረው በጎ ተግባር ጎንደር የታላቁ የአማራነት የባሕልና የሰላም ተምሳሌት ማሳያ መኾኑን ተናግረዋል።
“ጎንደር ባይተዋርነትን ታርቃለች፣ አብሮነት እና ፍቅርን ታስተምራለች፤ ከጎንደር ከራቁ ትናፈቃለችም” በማለትም የአካባቢው ማኅበረሰብ ያለውን የእንግዳ ተቀባይነት የቆየ እሴት አወድሰዋል።
ጎንደር የሀገር ፍቅር ነው የምትሰጠው ያሉት ሚኒስትሩ በጎንደር ውስጥ ሙሉ ኢትዮጵያ ትገኛለች በማለት መስክረዋል። የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የቃል ኪዳን ቤተሰብ የኢትዮጵያን አንድነት እና አብሮነት ለማጽናት ትልቅ ተምሳሌት ነውም ብለዋል።
የመድረኩ ዓላማ የጎንደር ዩኒቨርሲቲን መልካም ተሞክሮ በመቅሰም ኢትዮጵያን ለማጽናት እና እኛነትን ለማጎልበት በማሰብ የተካሄደ መኾኑን ያነሱት ሚኒስትሩ በሀገሪቱ በሚገኙ ሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች ይሄ መልካም ተግባር ሊጀምር እንደሚገባ መልዕክት አስተላልፈዋል።
የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ምክትል ከንቲባ ደብሬ የኋላ ጎንደር ዩኒቨርሲቲ እና የጎንደር ማኅበረሰብ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች መኾናቸውን ጠቅሰው ይህ አይነቱ ተግባር አንድነትን በማጽናት፣ አብሮነትን ለማስቀጠል እና የሀገርን ሰላም ለማስጠበቅ የሚያግዝ እንደኾነም ተናግረዋል።
በመርሐ ግብሩ የተገኙት የጎንደር ከተማ ነዋሪዎች በበኩላቸው አብሮነትን ለማጠናከር ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ወደ ጎንደር ዩኒቨርሲቲ የሚገቡ አዲስ ተማሪዎችን ልክ እንደ ልጆቻቸው በመቀበል የጀመሩትን ተግባር አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አስታውቀዋል።
ዘጋቢ ያየህ: ፈንቴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!