“በግልጽ ችሎት መዳኘት ሕግ መንግሥታዊ መሠረት ያለው የዜጎች መብት ነው” አቶ ቴዎድሮስ ምህረት

8

ባሕር ዳር: ሐምሌ 13/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሕንጻ ዕድሳት፣ የማስፋፊያ እና የዲጂታላይዜሽን ሪፎርም ሥራዎችን እያስመረቀ ነው።

በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፣ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ቴዎድሮስ ምህረት፣ የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ፣ የአማራ ክልል ምክር ቤት አፈጉባዔ ፋንቱ ተስፋዬን ጨምሮ ሌሎች የፌደራል እና የክልል ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል።

በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ቴዎድሮስ ምህረት በሀገረ መንግሥት ግንባታ ውስጥ ፍርድ ቤቶች የመንግሥትን መኖር አስፈላጊ ያደረጉ የሕግ እና የሥርዓት መስፈን ማረጋገጫዎች ናቸው ብለዋል።

የነጻነት መከበር፣ የማኅበራዊ ሥርዓት መጠበቅ፣ የኢኮኖሚ እድገት፣ የፍትሕ ሥርዓቱ መስፈን እና የሕግ የበላይነት መረጋገጥ እንዲኖር ነጻ እና ገለልተኛ ፍርድ ቤቶች እንዲኖሩ ግድ ይላል ነው ያሉት። ሁሉም ሰዎች በሕግ እንዲገዙ እና ከሕግ በታች እንዲኾኑ፣ በሕግ ፊት እኩል እንዲስተናገዱ፣ የሚያስችል ሥርዓት መዘርጋት የሚጠበቅ ነው ብለዋል። ኀላፊነቱን ሊሸከም የሚችል ተቋም እና የሰው ኃይል ግንባታ አስፈላጊ መኾኑንም ተናግረዋል።

ፍርድ ቤቶች የተጣለባቸውን ኀላፊነት መወጣት እንዲችሉ የሁሉንም አካላት ትብብር ይሻሉ ነው ያሉት። ፍርድ ቤቶች ያሉባቸውን ጉድለቶች ለመሙላት የማሻሻያ ሥራዎች እየተሠሩ መኾናቸውንም ገልጸዋል። የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሠራው ሥራ በግልጽ የሚታወቁ ነባር ችግሮችን የሚፈታ ብቻ ሳይኾን ወደ ሚፈለገው ግብ ለመድረስ ትክክለኛውን መንገድ መያዛችን ማረጋገጫ ነው ብለዋል።

ሥራው የተከናወነበት ፍጥነት፣ ጥራት እና ባለድርሻ አካላት ያሳዩት ትብብር አርዓያ ኾኖ የሚጠቀስ መኾኑን ገልጸዋል። ነጻ የዳኝነት ሥርዓትን ለማሳካት የሁሉም ድርሻ እንደሚጠይቅ ተናግረዋል። የክልሉ ምክር ቤት እና የክልሉ መንግሥት ላደረገው ድጋፍ እና እርምጃ አመስግነዋል።

ሌሎች ክልሎችም ከአማራ ክልል ልምድ እንዲወስዱ አደራ ብለዋል። ፍርድ ቤቶችን ለተቋቋሙለት ዓላማ በሚመጥን መልኩ ማዘጋጀት ይገባል ነው ያሉት። “በግልጽ ችሎት መዳኘት ሕገ መንግሥታዊ መሠረት ያለው የዜጎች መብት ነው” ብለዋል።

ፍርድ ቤቶች በግልጽ ችሎት ሥራቸውን ለማከናወን የሥራ ቦታቸውን ማመቻቸት አለባቸው ነው ያሉት። የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ያሳየው ተግባር ሊመሰገን ይገባል ብለዋል። የማስቻያ ቦታዎችን ማመቻቸት ብቻ ሳይኾን በቴክኖሎጂ የማስደገፍ ሥራም ተሠርቷል ነው ያሉት።

የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ የለወጥ ሥራዎች በጋራ እና በትብብር የተገኘ ወጤት መኾኑንም ገልጸዋል። ፈተናዎችን ለመፍታት በጋራ መሥራት እንደሚገባም ተናግረዋል።

የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሲያደርግ የነበረውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ገልጸዋል። የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በጠቅላይ ፍርድ ቤቱ የታየውን የለውጥ ሥራዎች እስከታች እንዲያወርድም አደራ ብለዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ምቹ የሥራ አካባቢ መፍጠር ቅንጦት ሳይኾን የዜጎችን በግልጽ ችሎት የመዳኘት መብት የማክበር እና የማስከበር ሕገ መንግሥታዊ ግዴታ ነው” አቶ ዓለምአንተ አግደው
Next article“ፍርድ ቤቶችን መደገፍ ሕዝብን መደገፍ ነው” ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ