“ምቹ የሥራ አካባቢ መፍጠር ቅንጦት ሳይኾን የዜጎችን በግልጽ ችሎት የመዳኘት መብት የማክበር እና የማስከበር ሕገ መንግሥታዊ ግዴታ ነው” አቶ ዓለምአንተ አግደው

17

ባሕር ዳር: ሐምሌ 13/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሕንጻ ዕድሳት፣ የማስፋፊያ እና የዲጂታላይዜሽን ሥራዎችን እያስመረቀ ነው።

በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፣ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ቴዎድሮስ ምህረት፣ የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ፣ የአማራ ክልል ምክር ቤት አፈጉባዔ ፋንቱ ተስፋዬን ጨምሮ ሌሎች የፌደራል እና የክልል ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል።

በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ዓለምአንተ አግደው በግልጽ ችሎት የመዳኘት፣ ተደራሽ፣ ቀልጣፋ፣ ወጪ ቆጣቢ፣ ወጥነት እና ጥራት ያለው ውጤታማ የዳኝነት አገልግሎት ማግኘት የዜጎች መብት ነው ብለዋል። ከዚህም ባሻገር እንዲሁ አይነት ዳኝነት የኅብረተሰቡ የዘወትር መሻት መኾኑን ተናግረዋል።

በግልጽ ችሎት የመዳኘት መብትን እውን ለማድረግ የችሎት አዳራሾችን ምቹ ማድረግ ይገባል ነው ያሉት። የዳኝነት አሰጣጡን በቴክኖሎጂ በማስደገፍ የባለጉዳዮችን ርካታ ያረጋገጡ እና በኅብረተሰቡ አመኔታ የተቸራቸው ፍርድ ቤቶችን መገንባት ቀዳሚ ተግባር ነው ብለዋል።

የመጨረሻ የመብት ማስከበሪያ ለኾነው የዳኝነት አካል ምቹ የሥራ አካባቢ መፍጠር ቅንጦት ሳይኾን የዜጎችን በግልጽ ችሎት የመዳኘት መብት የማክበር እና የማስከበር ሕገ መንግሥታዊ ግዴታ መኾኑን ተናግረዋል።

የዳኝነት ሙያን ክብር ከፍ በማድረግ የሕግ የበላይነትን እና ሰብዓዊ መብቶችን ለማክበር እና ለማስከበር ምቹ እድልን የመፍጠር ሂደት ነው ብለዋል። ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሦስተኛው የክልሉ መንግሥት አካል እና የመጨረሻው የመብት ማስከበሪያ ተቋም ኾኖ ሳለ የዳኝነት አካሉን እና የሕዝባችንን ክብር በማይመጥን፣ የሥራ ተነሳሽነት ስሜትን በሚጫጫን ምቹ ባልኾነ የሥራ ከባቢ ውስጥ ኾኖ የዳኝነት አገልግሎት ሲሰጥ ቆይቷል ነው ያሉት።

የዳኝነት አገልግሎት ሲሰጥባቸው የነበሩ ችሎቶች እና ቢሮዎች ለፍትሕ እና ርትዕ ቀናኢ አመለካከት ላለው ሕዝባችን ክብር ፈጽመው የማይመጥኑ ነበሩ ብለዋል። የዳኞችን ክብርም የሚመጥን እንዳልነበረ አስታውሰዋል። ወደ ኀላፊነት ከመጡበት ጊዜ ጀምሮ የዳኝነት ሥርዓቱን እና የሕዝብን ክብር የሚመጥን ሥራ ለመሥራት ጥረት መደረጉን ተናግረዋል።

በአጭር ጊዜ ውስጥ የሕንጻ እድሳት፣ የማስፋፊያ ግንባታ እና የፍርድ ቤቶች ዲጂታላይዜሽንና የሕንጻው መግቢያ ውጫዊ ቦታ መሠራቱንም ገልጸዋል።

በታችኛው ያሉ ፍርድ ቤቶች በማይመች መልኩ አገልግሎት እየሰጡ መኾናቸውን አንስተዋል። ይሄን ለመቀየር መሥራት እንደሚጠበቅም ተናግረዋል። የወረዳ ፍርድ ቤቶችን እና ዲጂታላይዜሽንን ምቹ ለማድረግ ሁሉም ባለድረረሻ አካል ድጋፍ እንደሚያደርግ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

የፍትሕ አገልግሎት በአንድ ተቋም ተጀምሮ የማይጠናቀቅ መኾኑን የተናገሩት ፕሬዝዳንቱ ይህን በማመን የጠቅላይ ፍርድ ቤቶች የትብብር ጽሕፈት ቤት ተቋቁሞ የዳኝነት እና የፍትሕ አካላትን ጥምረት በበላይነት እንዲያስተባብር መሠራቱን አንስተዋል።

በጋራ ማቀድ እና መሥራት ከተቻለ የክልሉን የፍትሕ አገልግሎት ማሻሻል እንደሚቻል አይተናል ነው ያሉት።

ሥራው በስኬት እንዲጠናቀቅ ድጋፍ ላደረጉ ሁሉ ምስጋና አቅርበዋል። የዳኝነት ሥርዓቱ ላይ የሚታዩ ችግሮችን ለመፍታት በትኩረት እየሠሩ መኾናቸውን አመላክተዋል። የፍርድ ቤቶችን ሚና በመገንዘብ ነጻ እና ገለልተኛ የዳኝነት ሥርዓት መገንባት ይገባል ነው ያሉት።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleአልማ በ17 ሚሊዮን ብር ያስገነባቸውን ተቋማት አስመረቀ።
Next article“በግልጽ ችሎት መዳኘት ሕግ መንግሥታዊ መሠረት ያለው የዜጎች መብት ነው” አቶ ቴዎድሮስ ምህረት