አልማ በ17 ሚሊዮን ብር ያስገነባቸውን ተቋማት አስመረቀ።

4

ጎንደር፡ ሐምሌ 13/2017 ዓ.ም (አሚኮ) አማራ ልማት ማኅበር (አልማ) በጎንደር ከተማ አንድ የቅድመ መደበኛ፣ ሁለት የመደበኛ ትምህርት ቤቶች እና አንድ ለወጣቶች የሥራ ዕድል መፍጠሪያ ሸድ አስመርቆ ለአገልግሎት ክፍት አድርጓል።

የጎንደር አልማ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ዳይሬክተር ይላቅ አለምሰገድ ለአገልግሎት ክፍት የኾኑ ፕሮጀክቶች 17 ሚሊዮን ብር ወጭ የተደረገባቸው መኾናቸውን አንስተዋል።

የጎንደር አልማ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት በ2015 ዓ.ም ራሱን ችሎ ከተደራጀ ጀምሮ በጥሬ ገንዘብ፣ በጉልበት እና በሙያ ድጋፍ 190 ሚሊዮን የሚገመት ሃብት መሠብሠቡን ዳይሬክተሩ ጠቅሰዋል።

አልማ በጎንደር ከተማ 105 ሺህ ነባር አባላት እንዳሉትም ተነስቷል።

አልማ በ2018 ዓ.ም በጎንደር ከተማ 122 መማሪያ ክፍሎችን፣ ሁለት የጤና ኬላዎችን እና ሁለት የሥራ ዕድል መፍጠሪያ ሸዶችን ለመገንባት ዕቅድ መያዙ ተጠቅሷል።

የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ትምህርት መምሪያ ኀላፊ ስንታየሁ ነጋሽ አልማ አራት ትምህርትቤቶችን በማጠናቀቅ ለ2018 የትምህርት ዘመን ማድረሱን ተናግረዋል።

ማኅበረሰቡ አልማን በመደገፍ የነገ የልጆቹን ዕጣ ፈንታ ማስተካከል እንዳለበትም መምሪያ ኀላፊው አሳስበዋል።

የአልማ ሥራ አመራር ቦርድ አባል ታጀበ አቻምየለህ ማኅበሩ ከቅድመ መደበኛ እስከ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች፣ የጤና ተቋማት እና የሥራ ዕድል ፈጠራ ሸድ በመገንባት የክልሉን ሕዝብ ተጠቃሚ እያደረገ ነው ብለዋል።

በአዘዞ የተክለሃይማኖት ቀበሌ ዋና ሥራ አሥኪያጅ በአካባቢያቸው 100 በላይ አርሶ አደሮች ከመሬት ካሣ ከተከፈላቸው ገንዘብ 7 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር ለአልማ ማበርከታቸውን አብራርተዋል።

በገንዘቡም ከ4 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ ደረጃውን የጠበቀ ትምህርት ቤት መገንባቱ ተማሪዎችን ለማብቃት አስተዋጽኦው የጎላ ነው ተብሏል።

በቀጣይ ለሥራ ዕድል ፈጠራ ሸድ ለመገንባት በዝግጅት ላይ መኾኑም ተጠቅሷል።

ዘጋቢ፡- አገኘሁ አበባው

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋ

Previous articleከ69 ሺህ በላይ ለኾኑ ወጣቶች የሥራ እድል መፍጠሩን የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር አስታወቀ።
Next article“ምቹ የሥራ አካባቢ መፍጠር ቅንጦት ሳይኾን የዜጎችን በግልጽ ችሎት የመዳኘት መብት የማክበር እና የማስከበር ሕገ መንግሥታዊ ግዴታ ነው” አቶ ዓለምአንተ አግደው