
ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 12/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ሥራና ሥልጠና መምሪያ የ2017 በጀት ዓመት እቅድ አፈጻጸም እና የ2018 በጀት ዓመት እቅድ ትውውቅ እና የቀጣይ አቅጣጫዎች ላይ የውይይት መድረክ አካሂዷል።
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ሥራ እና ሥልጠና መምሪያ ኀላፊ ዘመነ አሰፋ በ2017 በጀት ዓመት “ሥራ ዕድል ፈጠራ ከዳቦ በላይ ነው” በሚል መሪ መልዕክት ንቅናቄ ውስጥ በመግባት ለበርካታ ወጣቶች የሥራ ዕድል እንዲፈጠርላቸው ጥረት ተደርጓል ብለዋል።
በ2017 በጀት ዓመት በከተማዋ ለሚገኙ ከ69 ሺህ በላይ ወጣቶች የሥራ እድል ተፈጥሮላቸዋል ነው ያሉት።
በበጀት ዓመቱ 1 ሺህ 900 በላይ ኢንተርፕራይዞችም ተቋቁመዋል ብለዋል።
ለወጣቶቹ ብድር፣ ሼድ እና ሌሎች አስፈላጊ ነገሮችን አመቻችተናል ነው ያሉት፡፡ ከ274 ሚሊዮን ብር በላይ ለተጠቃሚዎች ብድር መሰጠቱንም ገልጸዋል፡፡
በ2017 በጀት ዓመት የውሸት ሪፖርትን ለማስቀረት ሁሉም ማዕከሎች በሲስተም እንዲተሣሠሩ በማድረግ የሥራ እድል ፈጠራው ትክክለኛ መረጃ ላይ እንዲመሠረት መደረጉን ገልጸዋል። ተቋሙ ኹሉም እምነት የሚጥልበት፣ የሚተማመንበት እና ለወጣቶች ተጨባጭ የሥራ እድል የሚፈጥር ተቋም እንዲኾን ሥራዎች ተሠርተዋል፣ በቀጣይ ዓመትም ተጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት።
የባሕዳር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው በከተማዋ የሥራ እድል ከመፍጠር ባለፈ የከተማዋን ሰላም ማረጋገጥ ቁልፍ ተግባር ተደርጎ መሥራቱ ተናግረዋል።
እቅድን ወደ ተግባር በመቀየር ለውጥ እያመጡ ካሉ ተቋማት ሥራ እና ሥልጠና መምሪያ አንዱ መኾኑን የጠቆሙት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ለዚህ ለውጥ እና ውጤት መሪዎችን እና ባለሙያዎችን አመሥግነዋል።
ለወጣቶች በተሻለ መንገድ መልስ እየሰጠን እንገኛለን ብለዋል። በከተማዋ ያሉ ወጣቶች በኢንዱስትሪ እና በሌሎች ዘርፎች እንዲሰማሩ ውጤታማ ሥራ መሠራቱንም አስታውቀዋል። የወጣቶቹ ሥራ እድል ፈጠራ በተያዘው ክረምት ጀምሮ በትልቁ የርብርብ ማዕከል ይኾናል ብለዋል።
የአማራ ክልል ሥራና ሥልጠና ቢሮ ኀላፊ ስቡህ ገበያው (ዶ.ር) በክልሉ ክህሎት መር የሥራ ፈጠራ ላይ ትኩረት ተደርጎ እየተሠራ እንደኾነ ገልጸዋል፡፡ ሥራ እድል በልቶ ማደር መኾን የለበትም ያሉት ኀላፊው ያመረቱት ምርት ለክልላቸው፣ ለሀገራቸው እና ለራሳቸው የሚጠቅም መኾን አለበት ብለዋል።
የአማራ ክልል በቀውስ ውስጥ ኹኖም በሥራ እድል ፈጠራ በሀገር አቀፍ ደረጃ 3ኛ ደረጃን ይዞ አጠናቅቋል ያሉት ኀላፊው ለዚህ የባሕር ዳር ወጣቶችም ድርሻ እንዳለበት ገልጸዋል፡፡
የሥራ እድል በመፍጠር ተሸላሚ የኾነው የዳግማዊ ምኒልክ ክፍለ ከተማ ሥራና ሥልጠና ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ዘላለም ደሳለው ለሽልማት ያበቃን በክፍለ ከተማው ያሉትን ፀጋዎችን ለይተን ወጣቶችን ወደ ሥራ በማሰማራታችን ነው ብለዋል። ሽልማቱም ለቀጣይ ዓመት ከዚህ በላይ ሥራ ሠርተን ውጤታማ እንድንኾን ያግዘናል ነው ያሉት።
የሥራ እድል ከተፈጠረላቸው ኢንተርፕራይዞች ውስጥ የአገልግል ኢኮ ፓኬጂንግ ሶሊዩሽን የወረቀት እና የወረቀት ምርቶች ማምረቻ ኀላፊ ወጣት ዮሐንስ አባቡ ከተለያዩ ተረፈ ምርቶች ወረቀቶችን፣ ደብተሮችን፣ የወረቀት ከረጢቶችን በማምረት ለተጠቃሚዎች በማድረስ ተጠቃሚ መኾናቸውን ተናግሯል፡፡ ለቀጣይም ብራንድ የኾኑ የወረቀት ምርቶችን በስፋት በማምረት እና ባሕርዳር ከተማን ከፕላስቲክ ብክለት ነፃ ለማድረግ ማቀዳቸውን ተናግሯል፡፡
በበጀት ዓመቱ የተሻለ አፈጻጻም ላስመዘገቡ የማዕከል እና የተቋሙ ባለሙያዎች እና የተሻለ እንቅስቃሴ የነበራቸው ኢንተርፕራይዞች እውቅና ተሰጥቷቸዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን