
ደሴ፡ ሐምሌ 12/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በደቡብ ወሎ ዞን ተሁለደሬ ወረዳ የተገነባው የ2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት ኾኗል።
በምርቃቱ ላይ የተገኙት የተሁለደሬ ወረዳ ነዋሪዎች ጀማል አወል እና ጣይቱ ኢብራሂም በአካባቢያቸው የ2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ባለመኖሩ ልጆቻቸውን ወደ ሐይቅ ከተማ በመላክ ያስተምሩ እንደነበር ተናግረዋል።
በቀበሌያቸው የተሠራው የሀራ አጠቃላይ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ልጆቻቸውን ከእንግልት እነሱንም ከወጭ እንደሚያድንላቸው ገልጸዋል።
የተሁለደሬ ወረዳ አሥተዳዳሪ ሠይድ አሕመድ ባለፉት ጥቂት ዓመታት በሰላም እጦት ምክንያት የትምህርት ሂደቱ ላይ እክል መፈጠሩን ገልጸዋል። በዚህም ትምህርት ቤቶች ለመማር ማስተማር ምቹ ሳይኾኑ ቆይተዋል ብለዋል።
ይህንን ችግር ለመቅረፍ በትኩረት እየተሠራ መኾኑን የተናገሩት አሥተዳዳሪው በወረዳው ሦሥት የአንደኛ ደረጃ እና አንድ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መገንባት ተችሏል ነው ያሉት።
የደቡብ ወሎ ዞን ትምህርት መምሪያ ኀላፊ ዓለምነው አበራ በዞኑ በ1 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር ወጭ 192 ትምህርት ቤቶች ላይ ግንባታ እየተከናወነ መኾኑን ጠቅሰዋል።
በተሁለደሬ ወረዳ የተሠራው የሀራ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት 43 ሚሊዮን ብር ወጭ እንደተደረገበት አስታውቀዋል።
በዞኑ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እጥረትን ለመቅረፍ እየተሠራ መኾኑን የገለጹት ኀላፊው ማኅበረሰቡ እያሳየ ያለው ትብብር የሚመሠገን ነው ብለዋል።
የደቡብ ወሎ ዞን ዋና አሥተዳዳሪ አሊ መኮንን በዞኑ ከ12 ቢሊዮን ብር በላይ በኾነ ወጭ የተለያዩ የልማት ፕሮጀክቶች እየተሠሩ መኾኑን ጠቅሰዋል። ከእነዚህም ውስጥ የትምህርት ቤት ግንባታ በትኩረት እየተሠራበት እንደኾነ ተናግረዋል።
በተያዘው የክረምት ወቅት የትምህርት ቤት ደረጃዎችን ለማሻሻል ይሠራል ነው ያሉት። የክረምት በጎ ፈቃድ ሥራውም አንዱ ትኩረት የሚያደርገው በትምህርት ዘርፍ ላይ መኾኑንም አመላክተዋል።
ዘጋቢ:-ሕይወት አስማማው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን