የአማራ ክልል መሬት ቢሮ የመሬት መረጃ አያያዝ ሥርዓትን ለማዘመን እየሠራ ነው።

19

ባሕር ዳር: ሐምሌ 12/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ምክር ቤት የግብርና፣ አካባቢ ጥበቃ እና የውኃ ሃብት ልማት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በሥሩ የሚከታተላቸውን የግብርና፣ የውኃ እና ኢነርጂ፣ የመስኖ እና ቆላማ አካባቢ፣ የመሬት ቢሮ እና የደን እና አካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን የ2017 በጀት ዓመት የሥራ አፈጻጸም እየገመገመ ነው።

ለቋሚ ኮሚቴው ሪፖርት ያቀረቡት የአማራ ክልል መሬት ቢሮ ኀላፊ ሲሳይ ዳምጤ በበጀት ዓመቱ የመሬት መረጃ አያያዝ ሥርዓቱን የማዘመን ሥራ እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል።

ከ345 ሺህ በላይ አርሶ አደሮች የሁለተኛ ደረጃ የይዞታ ማረጋገጫ ሰርተፊኬት ተሠጥቷቸዋል። ከ1 ነጥብ 3 ሚሊዮን በላይ ማሳ በሁለተኛ ደረጃ ካዳስተር በመመዝገብ ዲጂታላይዝድ ተደርጓል ብለዋል። 43 ሺህ 618 አርሶ አደሮች የሁለተኛ ደረጃ ደብተር በዋስትና በማስያዝ ከ853 ሚሊዮን ብር በላይ የብድር ተጠቃሚ መኾናቸውንም ነው የገለጹት።

ከ18 ሺህ 800 ሄክታር በላይ መሬት ለሥራ እድል ፈጠራ ማቅረብ ተችሏል። በበጀት ዓመቱ ከ104 ሺህ በላይ ዜጎች በቋሚነት፣ ለ839 ለሚኾኑ ዜጎች ደግሞ በጊዜያዊነት የሥራ ዕድል መፍጠር መቻሉንም አንስተዋል።

የተበታተነውን የአርሶ አደሮችን አሠፋፈር ወደ አንድ በማሰብሰብ በገጠር ኮሪደር ተጠቃሚ እንዲኾኑ የሚያስችል ሥራ መሠራቱንም ገልጸዋል። ይሁን እንጂ የከተማ መሬት ማዘመን ብዙ ያልተሠራበት መኾኑን ገልጸዋል።

ሌላኛው እንደ ችግር የተነሳው የልማት ተነሽዎች የካሳ፣ የትክ እና መልሶ ማቋቋም ሥራ ነው። ከ9 ነጥብ 7 ቢሊዮን በላይ ብር በፌደራል መንግሥት በክልሉ ለሚገኙ የልማት ተነሽዎች ያልተከፈለ ካሳ መኖሩን አንስተዋል። በቀጣይ ዓመት ትኩረት የሚሠጠው ጉዳይ መኾኑንም ገልጸዋል።

ዘጋቢ:- ዳግማዊ ተሠራ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleየወይዘሮ ስኂን ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ በተለያዩ የሙያ ዘርፎች ያሠለጠናቸውን ተማሪዎች አስመረቀ።
Next articleበተሁለደሬ ወረዳ ከ43 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ የተደረገበት ትምህርት ቤት ለአገልግሎት ክፍት ኾነ።