“ሁሉን ተመራመሩ፤ የሚጠቅመውን ያዙ” ዶክተር አብርሃም አስናቀ

16

ባሕር ዳር: ሐምሌ 12/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን አስመርቋል። በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የቀድሞው የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ምሩቅ ዶክተር አብርሃም አስናቀ ወደ ጎንደር ተመልሼ የወጣትነት ዘመኔን በማስታወሴ ደስ ብሎኛል ነው ያሉት።

መመረቅ ብዙ ትርጉም ያለው ነው፣ ወላጅ ይመርቃል፣ የሃይማኖት አባቶች ይመርቃሉ፣ ዩኒቨርሲቲም ይመርቃል፣ ምርቃት ተግባራዊ የሚኾነው ግን የተሰጣችሁን እውቀት በሥራ ላይ ስታውሉት ነው ብለዋል።

ከዩኒቨርሲቲ ተመርቃችሁ ይኾናል፣ ዕውቀት የማያልቅ ስለኾነ ገና ብዙ ይቀራችኋል ነው ያሉት። ከ56 ዓመታት በፊት በጤና መኮንንነት እንደተመረቁ ያስታወሱት ዶክተር አብርሃም ከመመረቅ በላይ የሚኾነው ሕዝብን ማገልገል ነው ብለዋል።

በዘመናቸው በገጠር እየተመላለሱ ሕዝብን ማገልገላቸውንም ተናግረዋል። ተመራቂዎች ከታች ወደላይ እንዲመለከቱም አሳስበዋል። “ሁሉን ተመራመሩ፣ የሚጠቅመውን ያዙ” ያሉት ዶክተር አብርሃም በማንኛውም ጊዜ ምርምር እንዲያደርጉ አሳስበዋል። ምርምር በላቦራቶሪ ብቻ ሳይኾን በማኅበረሰቡ ውስጥም አለ ብለዋል።

ዛሬም እየተማርኩ ነው፣ መማር ገና አያልቅም፣ ተማሪዎች የዩኒቨርሲቲ ትምህርት የመጨረሻ አይደለም፣ ትምህርት ያለው ማኅበረሰብ ውስጥ ነው ብለዋል በመልዕክታቸው። በማኅበረሰቡ ውስጥ እንዲማሩም አሳስበዋል።

ሌላኛዋ ከ56 ዓመታት በፊት የተመረቁት የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የቀድሞ ተመራቂ እና በኢትዮጵያ የመጀመሪያዋ ሴት ጤና መኮንን ዶክተር ተዋበች ቢሻው ይህን ሁሉ ዘመን ቆይቼ ይሄን እንዳይ ስላደረገኝ ፈጣሪዬን አመሰግናለሁ ብለዋል።

በጤናው ዘርፍ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ሲያደርጉ መቆየታቸውንም ተናግረዋል። የዛሬ ተመራቂዎች ችግሮችን እየተቋቋሙ እንዲሠሩ አሳስበዋል። ለእያንዳንዱ ቀን በቅንነት እንዲሠሩም አስገንዝበዋል። ትምህርት ለሁሉም ነገር መሠረት ነው ያሉት ዶክተር ተዋበች ትምህርት ትህትናን ያላብሳል፣ ለዚህ ያበቃን ማኅበረሰብ ማገልገል ትልቅ ክብር እና ጸጋ ነው ብለዋል።

የሚያጋጥሟችሁ እንቅፋቶች መንደርደሪያ እንጂ ተስፋ አስቆራጭ እንዳይኾንባችሁ አደራ እላችኋለሁ ነው ያሉት። ማኅበረሰቡን በቅንነት እንዲያገለግሉም አሳስበዋል።

ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleሐሰተኛ የትምህርት ማስረጃን እያጣራ መኾኑን የአማራ ክልል ሲቭል ሰርቪስ እና የሰው ሀብት ልማት ኮሚሽን ገለጸ።
Next articleየወይዘሮ ስኂን ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ በተለያዩ የሙያ ዘርፎች ያሠለጠናቸውን ተማሪዎች አስመረቀ።