ሐሰተኛ የትምህርት ማስረጃን እያጣራ መኾኑን የአማራ ክልል ሲቭል ሰርቪስ እና የሰው ሀብት ልማት ኮሚሽን ገለጸ።

25

ባሕር ዳር: ሐምሌ 12/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ምክር ቤት የሰው ሀብት አሥተዳደር እና ቱሪዝም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በሥሩ የሚቆጣጠራቸውን እና የሚደግፋቸውን ተቋማት የ2017 በጀት ዓመት የሥራ አፈጻጸም እየገመገመ ነው።

የአማራ ክልል ሲቭል ሰርቪስ እና የሰው ሀብት ልማት ኮሚሽን ኮሚሽነር ባንችዓምለክ ገብረማርያም በክልሉ ከ500 ሺህ በላይ የመንግሥት ሠራተኞች መኖራቸውን ገልጸዋል።

ኮሚሽኑ ሐሰተኛ የትምህርት ማስረጃን እያጣራ ይገኛል ያሉት ኮሚሽነሯ በሂደቱም ሐሰተኛ ማስረጃ የተገኘባቸው የመንግሥት ሠራተኞች መኖራቸውን አስታውቀዋል።

ሐሰተኛ የትምህርት ማስረጃዎችን የማጣራት ሂደቱ የተወሳሰበ በመኾኑ የሁሉንም የጋራ ርብርብ እና እገዛ ይጠይቃል ነው ያሉት።

ኮሚሽኑ በግጭት ምክንያት ለወደሙ ተቋማት በክልሉ መንግሥት በተመደበ ገንዘብ የተቋማት የጥገና ሥራ ማከናወኑን ተናግረዋል።

ሴቶችን እና አካል ጉዳተኞችን በአካቶ ትግበራ የማሳተፍ ክንውኑ ውጤታማ በመኾኑ ዕቅዱን ሙሉ በሙሉ ማሳካት መቻሉን ተናግረዋል።

በቀጣይ ወጣቱ ትውልድ የመንግሥት መሥሪያ ቤትን እንዲቀላቀል አስቻይ ኹኔታዎች እየተመቻቸ መኾኑንም አብራርተዋል።

በበጀት ዓመቱ በቢሮው የሕጻናት ማቋያ በመሠራቱ በተለይ ሴት ሠራተኞች ተረጋግተው ሥራቸውን እንዲያከናውኑ አድርጓል ብለዋል። ይህን ተሞክሮም ወደ ዞን እንዲወርድ መደረጉን ጠቁመዋል።

ሙስናን ለመከላከል ታች ድረስ በዕቅድ የተደገፈ ሥራ ማከናወኑን ተናግረዋል።

በሠራተኞች የሚቀርቡ ቅሬታዎችን በመቀበል እና በሚመለከታቸው ክፍሎች በማየት አሥተዳደራዊ ምላሽ መሰጠቱን ገልጸዋል።

ዘጋቢ:- ሙሉጌታ ሙጨ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleጉዳት የደረሰባቸውን ትምህርት ቤቶች መልሶ እየገነባ መኾኑን የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ አስታወቀ።
Next article“ሁሉን ተመራመሩ፤ የሚጠቅመውን ያዙ” ዶክተር አብርሃም አስናቀ