
ባሕር ዳር: ሐምሌ 12/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ምክር ቤት የሴቶች፣ ሕጻናት፣ ወጣቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ የሚከታተላቸውን ተቋማት የ2017 በጀት ዓመት የእቅድ አፈጻጸም እየገመገመ ነው።
የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ በ2017 በጀት ዓመት ያከናወናቸውን ዋና ዋና ተግባራት የእቅድ አፈፃፀም ለቋሚ ኮሚቴው አቅርቧል።
ሪፖርቱን ያቀረቡት የቢሮው ምክትል ኀላፊ መኳንንት አደመ በበጀት ዓመቱ ልዩ ልዩ እቅዶችን አዘጋጅቶ ወደ ተግባር መገባቱን፣ ደረጃውን የጠበቀ የሕጻናት ማቆያ የማደራጀት፣ በቢሮው ያጋጥም የነበረውን የውኃ እጥረትን መፍታት መቻሉን ገልጸዋል።
ዘመናዊ ቴክኖሎጅን ከመጠቀም አንጻር ቤተ መጽሐፍት ዲጂታል ማድረግ መቻሉን ገልጸዋል። የ8ኛ እና የ6ኛ ክፍል የተማሪዎች ምዝገባ እና ፈተናዎችን ከእጅ ንክኪ ነፃ በማድረግ በቴክኖሎጂ ለማረም ጥረት ተደርጓል ብለዋል።
በትምህርት ሚኒስቴር አማካኝነት 45 ትምህርት ቤቶች ሙሉ በሙሉ ተገንብተው መጠናቀቃቸውን ገልጸዋል። 12 ሞዴል የኾኑ የቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች መገንባታቸውን አንስተዋል።
በበጀት ዓመቱ የተሻለ የፕሮጀክቶች አፈጻጸም መከናወኑ በሪፖርቱ ተመላክቷል። ከአልማ ጋር በመተባበር በርካታ ትምህርት ቤቶች እየተገነቡ መኾኑንም ጠቁመዋል።
ሀገር አቀፍ እና ክልል አቀፍ ፈተናዎችን በተሻለ ውጤት ለማጠናቀቅ የሚያስችል ሰፊ የማጠናከሪያ ትምህርቶች መሠጠቱንም ገልጸዋል።
የመምህራን እና የትምህርት ቤት አመራሮች የሙያ ፈቃድ አሰጣጥ እና እድሳት በቀጣዩ ዓመት ወደ ተግባር ለማስገባት የሚያስችል የግንዛቤ ፈጠራ መሠራቱንም ገልጸዋል።
የጎልማሶች እና መደበኛ ያልኾነ ትምህርትን ተደራሽ ለማድረግ የተሠሩ ሥራዎች መኖራቸውንም ተናግረዋል።
የሥርዓተ ትምህርትን ተገቢነት እና ጥራትን ለማሻሻል በ12 የሙያ ዓይነቶች የብቃት፣ የይዘት ፍሰት እና የተማሪ ሞጁሎች መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።
የመልካም አሥተዳደር ችግሮችን በመለየት ለመፍታት ከፍተኛ ሥራ መሠራቱን አስታውቀዋል። ቢሮው የተመደበለት በጀትንም በአግባቡ መጠቀም መቻሉንም ነው የገለጹት።
የትምህርት ፍትሐዊነትን እና ተደራሽነትን በማሻሻል በኩል እጥረቶች ማጋጠሙን ምክትል ቢሮ ኀላፊው አንስተዋል። የልዩ ፍላጎት ተማሪዎች ለመለየት የባለሙያ እጥረት፣ የኅብረተሰቡ ግንዛቤ ዝቅተኛ መኾን፣ ትምህርት ቤቶቹ ለአካል ጉዳተኞች ተደራሽ አለመኾን ለዝቅተኛ አፈጻጸሙ በምክንያትነት አንስተዋል።
የትምህርት ቤት አመራሮችን እና መምህራንን በክረምት ማሠልጠን፣ የሥነ ልቦና ሥልጠና መሥጠት፣ ጉዳት የደረሰባቸውን ትምህርት ቤቶችን መልሶ መገንባት እና በቁሳቁስ ማጠናከር፣ ለትምህርት የደረሱ ሕጻናት ወደ ትምህርት ቤት እንዲመጡ ማድረግ ቢሮው በትኩረት የሚሠራቸው ተግባራት መኾናቸውን አቶ መኳንንት አመላክተዋል።
ዘጋቢ:- አሰፋ ልጥገበው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን