
አዲስ አበባ፡ ሐምሌ 12/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የ2017 የገቢ ዘመን ተጨባጭ ውጤት የተመዘገቡበት እና የስኬት ዓመት መኾኑን የገቢዎች ሚኒስቴር ገልጿል።
የገቢዎች ሚኒስትር አይናለም ንጉሴ የገቢ ዘመኑ ፓርቲው ባስቀመጠው አቅጣጫ መሠረት ውጤታማ የገቢ አሠባሠብ ሥርዓት የተተገበረበት እና በዚህም ውጤት የተመዘገበበት እንደነበረ ነው የተናገሩት።
ለስኬት መብቃት የተቻለውም የፓርቲውን ተልዕኮ በመገንዘብ ለስኬቱ ርብርብ በመደረጉ ነው ብለዋል ሚኒስትሯ።
ተቋሙ ፓርቲው እና መንግሥት የሰጠውን ታክስን የመሠብሠብ ተልዕኮን በድል መወጣቱን ነው ያብራሩት።
የተገኘውን ስኬት በማጠናከር ሀገራዊ ብልጽግናን ለማሳካት የኢኮኖሚ አቅምን ማጎልበት የግድ ነው ብለዋል።
የተመዘገቡ ስኬቶችን ተደማሪ በማድረግ ሀገራዊ ብልጽግናን ለማሳካት የ2018 በበጀት ዓመት ዕቅድን በኅብረት እና በትብብር መሥራት እንደሚገባ ነው የጠቆሙት።
የኢፌዴሪ ጉምሩክ ኮሚሽን ኮሚሽነር ደበሌ ቃበታ በበጀት ዓመቱ ታክስ የመሠብሠብ አቅምን የሚያጠናክሩ እና የገቢ ሥርዓቱን በሚፈትኑ ላይ ሕግን የማስከበር እና ተቋምን የማዘመን ተግባራት የተከናዎኑበት መኾኑንም ገልጸዋል።
ተቋሙ ዜጎች ሰው ሠራሽ እና ተፈጥሯዊ አደጋዎች በገጠማቸው ወቅት ደራሽ በመኾን ማኅበራዊ ኀላፊነቱን እየተወጣ መኾኑንም ኮሚሽነሩ አስታውቀዋል።
በቀጣይ ስኬቶችን በማጠናከር እና
የተመዘገበውን ውጤት በማስቀጠል ለፓርቲ ተልዕኮ ስኬት እና ለላቀ ውጤት የምንነሳበት ወቅት ነው ብለዋል ኮሚሽነሩ።
እየተካሄደ ባለው የፌዴራል ገቢዎች ሚኒስቴር እና ጉምሩክ ኮሚሽን የብልጽግና ፓርቲ ወረዳ የ2017 በጀት ዓመት አፈፃፀም ግምገማ ሚኒስትሮች እና የተለያዩ የሥራ ኀላፊዎች እንዲሁም የተቋማት ሠራተኞች ተገኝተዋል።
ዘጋቢ፦ ኢብራሂም ሙሐመድ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን