
ጎንደር፡ ሐምሌ 12/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ”ከካምፓችን ወደ ሕዝባችን” በሚል መርህ ለ7ኛ ጊዜ በሀገር መከላከያ ሠራዊት የሰሜን ምዕራብ ዕዝ የሠራዊት አባላት የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር አካሂደዋል።
የሰሜን ምዕራብ ዕዝ በጎንደር ከተማ አዘዞ ጠዳ ክፍለ ከተማ በሚገኘው ካምፕ ከፍተኛ የኮር እና የስታፍ መሪዎች በተገኙበት ነው የችግኝ ተከላ መርሐ ግብሩን ያካሄዱት።
በሀገር አቀፍ ደረጃ “በመትከል ማንሰራራት” በሚል መሪ መልዕክት የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር እየተከናወነ ነው።
በችግኝ ተከላው አሚኮ ያነጋገራቸው የሰሜን ምዕራብ ዕዝ ዋና አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ብርሀኑ በቀለ የመከላከያ ሠራዊቱ በጎንደር ከተማ ችግኝ ተከላን ጨምሮ በተለያዩ የበጎ አድራጎት ሥራዎች ላይ እየተሳተፉ መኾኑን ተናግረዋል።
ችግኝ መትከል የአየር ንብረት ሚዛንን በመጠበቅ ብሎም በድርቅ እና መሰል ጉዳቶች ከቦታ ቦታ የሚሰደዱ ዜጎችን ሕይዎት ለመታደግ የሚያስችል መኾኑንም ጄኔራል ብርሃኑ ገልጸዋል።
በሀገር መከላከያ ሠራዊት የሰሜን ምዕራብ እዝ 504ኛ ኮር 97ኛ ክፍለ ጦር ዋና አዛዥ ሌተናል ኮሎኔል ባቲ ቱኬ ችግኝ በመትከል የተራቆቱ መሬቶችን የመጠገን እና የአየር ንብረትን የመጠበቅ ኀላፊነት አለብን ብለዋል።
የመከላከያ ሠራዊት ከመደበኛ ሥራው ጎን ለጎን ከሚሠራቸው ዋና ዋና ተግባራት አንዱ እና ዋነኛው የችግኝ ተከላ እንደኾነም አብራርተዋል።
ኮሎኔል ባቲ ችግኞችን መትከል ብቻ ሳይኾን የጽድቀት መጠናቸው እንዲጨምር ልክ እንደተከላው ሁሉ የመንከባከብ ኀላፊነት እንዳለባቸውም ነው ያስረዱት።
ሰላምን ከማረጋገጥ ጎን ለጎን በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር በመሳተፋቸው ሀገራዊ ኀላፊነታቸውን እየተወጡ እንደኾነ በችግኝ ተከላ መርሐ ግብሩ ላይ የተሳተፉ የሠራዊቱ አባላት ተናግረዋል።
የመከላከያ ሠራዊት የሕዝብ ልጅ በመኾኑ ከመደበኛ ሥራው ውጭ በጉልበት፣ በገንዘብ እንዲሁም በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ድጋፍ ለማድረግ ሁሌም ዝግጁ እንደኾነ ከፍተኛ መሪዎቹ ጠቁመዋል።
ዘጋቢ፦ ተስፋዬ ጋሹ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን