በዘንድሮው መኸር ከ187 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለማግኘት እየተሠራ ነው።

20

ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 12/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ምክር ቤት የግብርና፣ አካባቢ ጥበቃ እና የውኃ ሃብት ልማት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በሥሩ የሚከታተላቸውን የግብርና፣ የውኃ እና ኢነርጂ፣ የመስኖ እና ቆላማ አካባቢ፣ የመሬት ቢሮ እና የደንና አካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን የ2017 በጀት ዓመት የሥራ አፈጻጸም እየገመገመ ነው።

ሪፖርት ካቀረቡት ተቋማት መካከል ግብርና ቢሮ አንዱ ነው። ሪፖርቱን ያቀረቡት የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ኀላፊ ቃልኪዳን ሽፈራው በበጀት ዓመቱ አዲስ የኤክስቴንሽን አደረጃጀት መፍጠር ላይ ትኩረት ተደርጎ መሠራቱን ገልጸዋል።

በ2016/17 የምርት ዘመን ከ170 ሚሊዮን በላይ ኩንታል ምርት መገኘቱን ገልጸዋል። በ2017/18 የምርት ዘመን ምርቱን በ10 በመቶ በማሳደግ ከ187 ሚሊዮን 540 ሺህ በላይ ኩንታል ለማግኘት እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል።
ምርታማነቱንም በሄክታር 32 ነጥብ 3 ኩንታል ወደ 34 ነጥብ 7 ኩል ለማሳደግ እየተሠራ መኾኑን ነው የገለጹት።

በበጀት ዓመቱ ግዥ ከተፈጸመው ስምንት ነጥብ ስምንት ማሊዮን ኩንታል ማዳበሪያ እስካኹን ከ5 ነጥብ 2 ሚሊዮን ኩንታል በላይ መሠራቱን ገልጸዋል።

ምርታማነትን ለማሳደግ በሽታን የሚቋቋሙ እና አዳዲስ ዝርያዎችን እና የቴክኖሎጅ ውጤቶችንም ወደ አርሶ አደሩ የማቅረብ ሥራ እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል።

በበጀት ዓመቱ ለማዘጋጀት ከታቀደው 20 ሚሊዮን ቡና እና ፍራፍሬ ችግኝ እስካኹን 18 ሚሊዮን በላይ ማዘጋጀት ተችሏል። ክልሉ በቡና እና በፍራፍሬ
የተሻለ አቅም ቢኖረውም በአቅሙ ልክ እየተመሠረተ አለመኾኑን ገልጸዋል።

በበጀት ዓመቱ 208 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት የበጋ መስኖ ስንዴ በማልማት
ከ7 ነጥብ 4 ሚሊዮን በላይ ኩንታል ምርት መገኘቱንም ምክትል ኀላፊው ገልጸዋል።

የተፈጥሮ ሃብት ሥራ በትኩረት ሲሠራ እንደነበር ምክትል ኀላፊው አቅርበዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleተመራቂ ተማሪዎች ጥሩ የማኅበረሰብ መሪ መኾን ይገባቸዋል።
Next articleየሚተከሉ ችግኞች የጽድቀት መጠናቸው እንዲጨምር የመንከባከብ ኀላፊነት አለብን።