
ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 12/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎቹን እያስመረቀ ነው። በምረቃ መርሐ ግብሩ ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት በኢፌዴሪ ትምህርት ሚኒስቴር የአሥተዳደር እና መሠረተ ልማት ዘርፍ ዋና ሥራ አሥፈጻሚ እና የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ተወካይ ሰለሞን አብርሃ (ዶ.ር) ኢትዮጵያ ለትምህርት ልዩ ትኩረት ሰጥታ እየሠራች እንደምትገኝ ገልጸዋል።
ባለፉት ዓመታት በትምህርት ዘርፉ ቀላል የማይባል ኢንቨስትመንት የተደረገበት እንደኾነም ነው የጠቆሙት።
በከፍተኛ ትምህርት ተደራሽነትን በማረጋገጥ ረገድ ውጤታማ ሥራ ተሠርቷል ያሉት ዶክተር ሰለሞን የትምህርት ጥራት ላይ ያለውን ክፍተት ለመሙላት ግን ብዙ ሥራ እንደሚጠይቅ ነው ያስገነዘቡት።
መንግሥት የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ በርካታ የሪፎርም ሥራ እያከናወነ እንደሚገኝም አስገንዝበዋል።
ይህንንም ለማረጋገጥ ተቋማትን በተልዕኮ የማደራጀት፣ የራስ ገዝ አሥተዳደርን መመሥረት፣ የተቋማትን የብቃት ደረጃ የማረጋገጥ ተግባር፣ የፈተና ሥርዓቱን የማዘመን ተግባር፣ የአመራር ሥርዓቱን የማብቃት፣ የምርምር አሥተዳደሩን የማጠናከር፣ የዲጂታል ትምህርትን የማስፋፋት ሥራ እና ሌሎች ተግባራት በትምህርት ሚኒስቴር በኩል እየተሠራ እንደኾነም ነው የጠቆሙት።
የተጀመሩት ሥራዎችም ውጤት እያመጡ እንደኾነም አብራርተዋል።
ኢትዮጵያ የረጅሙን የኋላቀርነት ምእራፍ አውልቃ ጥላ ወደ ዘመናዊው ዓለም ለመቀላቀል ረጅሙን ጉዞ ስለመጀመሯ ተናግረዋል።
በዚህ ሥራም የትምህርት እና የዩኒቨርሲቲዎች ሚና ከፍ ያለ ስለመኾኑ ጠቁመዋል።
ዩኒቨርሲቲዎች በሳይንስ እና በምርምር ሥራ ከፍ ያለ አበርክቶ መጫዎት እንደሚጠበቅባቸውም ነው ያብራሩት።
ይህን ለማሳካትም በሀገሪቱ ካሉ ዩኒቨርሲቲዎች መካከል አንጋፋው የጎንደር ዩኒቨርሲቲ አንዱ እንደኾነ ገልጸው በዚህም እየሠራ ያለው ሥራ ትልቅ መኾኑን ተናግረዋል።
ጎንደር ዩኒቨርሲቲ የምርምር ተቋም ለመኾን የሚያስፈልጉ መሠረታዊ ጉዳዮችን አሟልቶ የጀመረው ጉዞ የሚያስመሠግነው እንደኾነም ነው ያብራሩት።
ዩኒቨርሲቲው ሀገሪቱ የምትፈልገውን የተማረ የሰው ኀይል በማውጣት፣ ለብልጽግና ጉዞው የተሻለ አበርክቶ በመወጣት እና በምርምር ሥራ ከፍ ያለ ሥራ መሥራቱን አስገንዝበዋል።
ሳይንስ እና ቴክኖሎጅ ውዴታ ሳይኾን ግዴታ በመኾኑ ይህን ማዕከል አድርጎ መሥራት እንደሚገባም ጠቁመዋል።
ለውጡ ፈጣን ነው ከዓለም ጋር ለመቀላቀል በቴክኖሎጂ ማገዝ ያስፈልጋል ነው ያሉት።
በዚህ ረገድ ዩኒቨርሲቲዎች ቀዳሚ ኾነው መሥራት አለባቸውም ብለዋል።
ለተመራቂዎችም ያገኙት ዕውቀት ይህን ዓለም ለማሰስ የሚያገለግላቸው እንደኾነ ገልጸው ዕውቀት ብቻውን በቂ ባለመኾኑ በትጋት እና ዓለምን በማንበብ መንቀሳቀስ እና ጥሩ የማኅበረሰብ መሪ መኾን እንደሚገባቸውም መክረዋል።
ፈተናዎችን እንደ ዕድሎች በመውሰድ መሥራት ተመራቂዎች እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል።
በፈተናዎች መካከል ጥንካሬ የሚገኝ በመኾኑ ይህን ዕድል እንዲጠቀሙም ገልጸዋል ።
ዕውነተኛ ስኬት በሌሎች ላይ በጎ ተጽዕኖ መፍጠር እንደኾነም ጠቁመዋል።
ሩህሩህ እና ቅን በመኾን ችግሮችን መፍታት ከተመራቂዎች እንደሚጠበቅም ነው ያስረዱት።
አሁን ያገኙት ዕውቀት የእንጀራቸው እርሾ እንጅ በራሱ በቂ ባለመኾኑ በምርምር ሥራ ሀገራቸው እና ሕዝባቸው የሚጠብቀውን ውጤት በማምጣት ሀገርን ማበልጸግ እንደሚገባቸው አሳስበዋል።
በምሥጋናው ብርሃኔ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን