አሚኮ ለሰላም እና ለሃሳብ ብዝኃነት በልዩ ትኩረት ሠርቷል።

15

ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 12/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ምክር ቤት የሰው ሃብት አሥተዳደር እና ቱሪዝም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በሥሩ የሚቆጣጠራቸውን እና የሚደግፋቸውን ተቋማት የ2017 በጀት ዓመት የሥራ አፈጻጸም እየገመገመ ይገኛል።

የአሚኮ ዋና ሥራ አሥፈጻሚ ጋዜጠኛ ሙሉቀን ሰጥዬ ባቀረቡት የሥራ ክንውን አሚኮ ለሰላም እና ለሃሳብ ብዝኃነት መሥፈን ልዩ ትኩረት ሰጥቶ ሠርቷል ነው ያሉት።

ኮርፖሬሽኑ ክልሉ ወደ አንጻራዊ ሰላም እንዲመጣ፣ በሀገር አቀፍ ደረጃ የተጀመረው ሁሉን አቀፍ ምክክር ፍሬያማ እንዲኾን፣ የሐሳብ ብዝኃነት ስለሚኖረው ጠቀሜታ ሠርቷል ነው ያሉት።

እንደ ሀገር እና ክልል እየተከናወኑ ያሉ ፕሮጀክቶችን የግንባታ ክትትል፣ የተቋማት ሪፎርም በተመለከተ ልዩ ትኩረት በመሥጠት በስፋት መረጃን ለሕዝብ ማድረሱንም ጋዜጠኛ ሙሉቀን ተናግረዋል።

ኮርፖሬሽኑ የሀገርን ገጽታ አጉልተው የሚያሳዩ ዘገባዎችን በስፋት ማሠራጨቱንም አውስተዋል። ለሀገራዊ እሴት ግንባታ በተለያዩ የይዘት አማራጭ ሚዲየሞቹ ሠርቷል ብለዋል።

አሚኮ ሥራውን ዲጂታላይዝ በማድረግ፣ ከተቋማት ጋር በቅንጅት በመሥራት እና የሥራ ቦታዎችን ይበልጥ ምቹ በማድረግ ረገድ ጉልህ ሥራ ማከናዎኑንም አብራርተዋል።

የአማራ ክልል ኮሙኒኬሽን ቢሮ ኀላፊ መንገሻ ፈንታው (ዶ.ር) ባቀረቡት የሥራ ክንውን ደግሞ ክልሉ ገጥሞት ከነበረው የጸጥታ ችግር ወጥቶ አንጻራዊ ሰላም እንዲሰፍን የሚያስችሉ መረጃዎችን በተለያዩ መንገዶች ተደራሽ ተደርገዋል ብለዋል።

በክልሉ ውስጥ የተከናዎኑ ሁሉን አቀፍ ጉዳዮች በዓመታዊ መጽሐፍ ውስጥ በምሥል እና ጽሑፍ እንዲዘጋጁ መደረጉንም ተናግረዋል።

አኹን የተገኘው አንጻራዊ ሰላም እና እምርታዊ የልማት ክንውኖች አሚኮ እና የክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ ተናበው የሠሩት ሥራ ውጤት ነው ብለዋል።

በቱሪዝም በዓላት በርካታ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ጎብኝዎች ይታደሙ ዘንድ የገጽታ ግንባታ ሥራዎች መከናዎናቸውንም አብራርተዋል።

በሙሉጌታ ሙጨ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየጎንደር ዩኒቨርሲቲ የቀድሞ ተማሪዎችን በድጋሜ አስመረቀ።
Next articleተመራቂ ተማሪዎች ጥሩ የማኅበረሰብ መሪ መኾን ይገባቸዋል።