“ኪን ኢትዮጵያ፣ የኢትዮጵያ ማንሰራራት ብስራት” የመጀመሪያ ጉዞ ወደ ቻይና ሊደረግ ነው።

23

አዲስ አበባ: ሐምሌ 11/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የባሕልና ስፖርት ሚኒስቴር ከሻኩራ ፕሮዳክሽን ጋር በመተባበር ያዘጋጁት የባሕል እና የጥበብ ጉዞ ወደ ተለያዩ ሀገራት እንደሚደረግ ከዚህ ቀደም መገለጹ ይታወቃል።

ይህንንም አስመልክቶ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት፣ የባሕልና ስፖርት ሚኒስቴር፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እና ሌሎች አጋሮች ጋር በመኾን ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።

እንደ ሀገር “ጠጣር እና ገር” የሚሰኙ ብሔራዊ ኀይሎች አሉ ያሉት የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ተስፋሁን ጎበዛይ ገር የሚባለውን የጥበብ ኀይል በመጠቀም ኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ገፅታዋን ለዓለም ለመግለጥ እና ለማስተዋወቅ ተዘጋጅታለች ብለዋል።

ከኢትዮጵያ ጋር የውጭ፣ የንግድና የፋይናንስ ግንኙነት ወዳላቸው ሀገራት በመጓዝ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ.ር) የተቀመጠውን ኪነ ጥበብን በመጠቀም የሀገርን ገፅታ ለመላው ዓለም የማስተዋወቅ አቅጣጫ ለመተግበር አስፈላጊውን ሁሉ ይደረጋል ነው ያሉት።

ጉዞው የፊታችን እሑድ በቻይና ሁለት ከተሞች ማለትም ቤጂንግ እና ናንጂንግ ይጀምራል። ለዚህም በውጭ ጉዳይ ሚኒሥቴር በኩል መንግሥት ለመንግሥት ግንኙነት ተደርጓል።

በየሀገራቱ ያሉ የሚዲያ ተቋማትም ሽፋን የሚሰጡ ይኾናል ብለዋል አቶ ተስፋሁን። ጉዞው ኦፊሴላዊ እና በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ ሽኝት ተደርጎ በባሕልና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ የሚመራ እና የጎንዮሽ ውይይቶች እና ልምድ ልውውጦች የሚደረጉበት መኾኑን ገልጸዋል።

የባሕልና ስፖርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ነብዩ ባዬ ይህ ጉዞ የኢትዮጵያ መልክ የሚተዋወቅበት የሕዝብ ለሕዝብ ጉዞ ከተደረገበት ከ39 ዓመታት በኋላ የሚደረግ ነው ብለዋል። ይህም ቱሪዝምና ኢንቨስትመንት የሚተዋወቅበት ጉዞ እንደሚኾን ተገልጿል።

ጉዞው ቀጣይነት ያለው መኾኑንም ጠቁመዋል። ይህ ታሪካዊ አሻራ የሚጣልበት እና የማይቋረጥ ይኾናል ብለዋል። መንግሥት ለሰጠው ትኩረት እና የፖሊሲ ድጋፍ ሚኒስትር ዴኤታው ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

የሻኩራ ፕሮዳክሽንና የኪነ ጥበብ ቡድኑ መሪ አርቲስት ካሙዙ ካሳ በበኩሉ የኢትዮጵያን ባሕል፣ ሙዚቃ፣ አለባበስ እና ሌሎች መገለጫዎችን ለማሳየት አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት አድርገናል ብሏል።

70 የባሕል ቡድን አባላት በጉዞው እንደተካተቱ እና ለወራት ልምምድ ማድረጋቸውን አርቲስት ካሙዙ ገልጿል።

ይህ የመጀመሪያ ምዕራፍ ጉዞ ሐምሌ 13 ይጀመራል ተብሏል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበበጎ ተግባራት በመሳተፍ ለትውልድ የሚጠቅም ተግባር መሥራት ይገባል።
Next article“ሁለት ቤተሰብ የሚደግስላችሁ ተማሪዎች ዕድለኞች ናችሁ” አሥራት አጸደወይን (ዶ.ር)