በበጎ ተግባራት በመሳተፍ ለትውልድ የሚጠቅም ተግባር መሥራት ይገባል።

13

ገንዳ ውኃ፡ ሐምሌ 11/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በምዕራብ ጎንደር ዞን በመተማ ወረዳ ኮኪት ከተማ “በጎነት ለኢትዮጵያ ከፍታ” በሚል መሪ መልዕክት የበጎ አድራጎት ሥራዎች ተጀምረዋል።

በማስጀመሪያ መርሐ ግብሩ የክልል፣ የዞን እና የወረዳ ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል።

በአማራ ክልል ባሕል እና ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ኀላፊ አየለ አናውጤ (ዶ.ር) በአረንጓዴ አሻራ ኢትዮጵያን በማልበስ ለሚቀጥለው ትውልድ መልካም ነገሮችን ማስተላለፍ ይገባል ብለዋል።

በክረምቱ በጎ ፈቃድ ሁሉም ዜጋ የአቅመ ደካሞችን ቤት መሥራት እና ተማሪዎችን በቁሳቁስ በመደገፍ ለትውልድ የሚጠቅም ተግባር መሠራት እንዳለበትም ተናግረዋል።

ማኅበረሰቡ ሰላምን ከማስፈን ጎን ለጎን አካባቢውን ማልማት ይኖርበታልም ነው ያሉት።

የምዕራብ ጎንደር ዞን ዋና አሥተዳዳሪ እያሱ ይላቅ የአቅመ ደካማ ቤቶችን መገንባት ለዜጎች የበጎነት ተግባር እና የወገን አለኝታነት ማሳያ ተግባር ነው ብለዋል።

የአቅመ ደካሞችን ቤት መሥራት በራሱ ደስታን ይፈጥራል፤ ስለዚህ የእናቶችን ቤት ለመሥራት ሁሉም አካል መሳተፍ እንዳለበት ገልጸዋል።

በገንዘብ ብቻ ሳይኾን አቅም በፈቀደው መልኩ በጉልበትም ኾነ በሀሳብ መደጋገፍ እንደሚያስፈልግም አስገንዝበዋል።

አቅመ ደካማ እናቶችን ከሚያፈስ እና ጎርፍ ከሚሄድበት ቤት ማውጣት ያስፈልጋልም ብለዋል።

የመተማ ወረዳ ዋና አሥተዳዳሪ ግዛት ሰርፀ የዜጎች የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ተግባራትን በከተሞች እየተጀመሩ መኾናቸውን ተናግረዋል።

በበጎ ፈቃድ ሥራዎች የአቅመ ደካማ ቤቶችን መሥራት፣ በአረንጓዴ አሻራ ተግባር መሳተፍ፣ ደም መለገስ፣ ተማሪዎችን ማገዝ እና ሌሎች ሥራዎችን እንደሚያከናውኑ አስገንዝበዋል።

በክረምት በጎ ፈቃድ ለአቅመ ደካሞች አዲስ እና ነባር ቤቶችን እየሠሩ እንደኾነም አስረድተዋል።

በማንኛውም የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ንቅናቄ ሁሉም ማኅበረሰብ ተሳትፎውን አጠናክሮ እንዲቀጥልም መልዕክት አስተላልፈዋል።

ቤታቸው የተሠራላቸው እናት ወይዘሮ ትኩየ መስፍን “እኔን እንዳያችሁኝ ፈጣሪ እናንተን ይያቹሁ” በማለት የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል።

በተሠራላቸው በጎ ሥራ ከዝናብ እንደዳኑ ተናግረው ሌሎች እናቶችም ከዝናብ እንዲድኑ ማገዝ እንደሚገባ ነው ያስረዱት።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleየደቡብ ወሎ ዞን በአረንጓዴ አሻራ ሥራ ለፍራፍሬ ችግኞች ልዩ ትኩረት ሰጥቷል።
Next article“ኪን ኢትዮጵያ፣ የኢትዮጵያ ማንሰራራት ብስራት” የመጀመሪያ ጉዞ ወደ ቻይና ሊደረግ ነው።