የደቡብ ወሎ ዞን በአረንጓዴ አሻራ ሥራ ለፍራፍሬ ችግኞች ልዩ ትኩረት ሰጥቷል።

17

ደሴ: ሐምሌ 11/2017 ዓ.ም (አሚኮ) አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የተለያዩ የግብርና ሥራዎችን እየሠራ መኾኑን ወሎ ዩኒቨርሲቲ አስታውቋል።

የወሎ ዩኒቨርሲቲ ግብርና ኮሌጅ የማኅበረሰብ አገልግሎት የሙዝ ክላስተር ችግኝ ተከላ በደቡብ ወሎ ዞን ቃሉ ወረዳ አካሂዷል።

በተያዘው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር በዞኑ ከ200 ሚሊዮን በላይ ችግኝ እንደሚተከል የተናገሩት የደቡብ ወሎ ዞን ግብርና መምሪያ ኀላፊ አህመድ ጋሎ 1 ነጥብ 9 ሚልዮን የሚኾነው የፍራፍሬ ችግኝ መኾኑን ተናግረዋል።

በዛሬው እለት በወረዳው 034 ቀበሌ በኩታ ገጠም 20 ሺህ የተሻሻለ የሙዝ ችግኝ መተከሉን ገልጸዋል።

ወሎ ዩኒቨርሲቲ ከመማር ማስተማር ሥራው ባለፈ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የማኅበረሰብ አቀፍ የግብርና ሥራዎችን እየሠራ መኾኑን የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት አወል ሰይድ (ዶ.ር) ተናግረዋል።

1 ነጥብ 3 ሚልዮን ብር ወጭ በማድረግ ከደሴ ቲሹ ካልቸር ጋር በመቀናጀት 50 ሺህ የተሻሻሉ የሙዝ ዝርያዎች ማዘጋጀታቸውን የተናገሩት ፕሬዝዳንቱ 20 ሺህ የሚኾነው በዛሬው እለት መተከሉን ገልጸዋል።

ቀሪው 30 ሺህ ደግሞ በአርጎባ ብሔረሰብ ልዩ ወረዳ እንደሚተከል ገልጸዋል። በቀጣይም ከደሴ ቲሹ ካልቸር ጋር በመተባበር አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የተሻሻሉ የአትክልትና የፍራፍሬ ችግኞችን እንደሚያለሙ ገልጸዋል።

የተተከሉት የሙዝ ችግኞች ጸድቀው ምርት እስኪሰጡ ድረስ ዩኒቨርሲቲው ለአርሶ አደሮች ክትትል እና ድጋፍ እንደሚያደርግ ፕሬዝዳንቱ ተናግረዋል።

ቃሉ ወረዳ ለአትክልት እና ፍራፍሬ ልማት ምቹ የኾነ ሰፊ መሬት ቢኖረውም መልማት በሚገባው ልክ አለመልማቱን የተናገሩት ደግሞ የደቡብ ወሎ ዞን ዋና አሥተዳዳሪ አሊ መኮነን ናቸው።

የአካባቢውን ለም መሬት በመጠቀም የፍራፍሬ ልማት ላይ የተጀመረው ሥራ ጥሩ ውጤት እያሳየ መኾኑን የማንጎ ምርትን ምሳሌ በማድረግ ጠቅሰዋል።

በዛሬው ዕለት የተተከለው የተሻሻለ የሙዝ ችግኝ እና በቀጣይም የሚተከሉ ፍራፍሬዎችን በአግባቡ ተንከባክቦ ከሌላ አካባቢ የሚመጣውን የሙዝ ምርት በአካባቢው ምርት ለመተካት አርሶ አደሮች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጠንክረው መሥራት እንዳለባቸውም ዋና አሥተዳዳሪው ተናግረዋል።

አርሶ አደሮች ከልማቱ ጎን ለጎን የአካባቢውን ሰላም እንደ ተለመደው እንዲጠብቅም አሳሰበዋል። .

በኩታ ገጠም የተሻሻለ የሙዝ ችግኝ መትከላቸው ከዚህ በፊት ያለሙት ከነበረው የማሽላ እና የበቆሎ ምርት የተሻለ ጥቅም እንደሚያገኙበት ከዚህ በፊት ከተተከሉ የሙዝ ችግኞች ግንዛቤ መውሰዳቸውን የ034 ቀበሌ አርሶ አደሮች ተናግረዋል።

የተሻሻለው የሙዝ ችግኝ በዘጠኝ ወር ውስጥ ምርት የሚሰጥ በመኾኑ ምርጫቸው እንዳደረጉትም አርሶ አደሮቹ ገልጸዋል።

ዘጋቢ:- ሀያት መኮንን

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleሁለት ዓመታትን በአንታርክቲካ የኖሩት የጽናት ተምሳሌቶች
Next articleበበጎ ተግባራት በመሳተፍ ለትውልድ የሚጠቅም ተግባር መሥራት ይገባል።