
ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 11/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በዓለማችን ደቡባዊ ጫፍ የሚገኘውን አህጉር አንታርክቲካን የከፍታዎች ምድር ይሉታል። በጣም ቀዝቃዛማ፣ በጣም ነፋሳማ እና በጣም በረዷማ ስፍራ ስለኾነ ነው ይህ መጠሪያ የተቀጠለለት።
በስፋቱ አምስተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠ ክፍለ ዓለም ነው። ዝናብ ዝር የማይልበት ግን ደግሞ 90 በመቶ የሚኾነውን የምድራችንን ንፁሕ ውኃ በጉያው ሸክፎ የያዘ ነው። ከዜሮ በታች ኔጌቲቭ 89 ነጥብ 2 አማካይ ሙቀት ያለበት ምድር ነው።
አጥንት ሰርስሮ የሚገባው ብርድ እና ገላን የሚቆራርጠው እና የሚያከስለው ከባድ ነፋስ በስፍራው ለመኖር አይደለም ውሎ ለማደር ፈተና ነው።
በዚህ ከባድ ስፍራ 27 አባላቱን እየመራ 21 ለመተረክ የሚከብዱ የፈተና ወራትን ማሳለፍ የቻለ አንድ ብርቱ ሰው ግን በታሪክ ሥሙ ከፍ ብሎ እናገኛለን።
ብዙ ዓመታትን ወደኋላ ተሻግረን የአውሮፓውያንን 1914 ዓ.ም የታሪካችን መነሻ አድርገን ስንነሳ አየርላንዳዊው ሰር ኧርነስት ሻክልተን ደምቆ ይታያል። ይህ ሰው ለማድረግ አይደለም ለማሰብ የሚከብደውን አስቼጋሪውን የአንታርክቲካን ክፍለ ዓለም በመርከብ አቋርጣለሁ ብሎ ተነሳ። የጉዞው አባል የኾኑ 27 ሰዎችን አብሮ ይዞ ነበር የመርከብ ጉዟቸውን ወደ አንታርክቲካ የጀመሩት።
ሻክልተን ከቤተሰቦቹ የወረሰውን “በጽናት ማሸነፍ” የሚል መርሕ መነሻ በማድረግ የመርከባቸውን ሥም “ጽናት” የሚል መጠሪያ ሰጥቷት ነበር።
ሻክልተን የጸና ሕልም ይዞ አባላቱን እያበረታ ብዙ ወራትን ተጓዙ በጥር ወር 1915 ዓ.ም ላይ ግን “ጽናት” ከዚህ በላይ መጽናት የማትችለው ብርቱ እክል ገጠማት፣ ቸገራት፣ ጠበባት፣ ምጥ ኾነባት። በከባድ የበረዶ ግግር ተያዘች። ብዙ ወራትን ተጉዘው መጥተው ልመለስ የማይሉበት የምድር ክፍል ላይ ለመቆም ተገደዱ።
ቢጮሁ የማይሰማበት፣ ስልክ ደውየ እርዳታ ልጥራ የማይሉበት የመነነው የዓለም ክፍል ላይ እና አፈር እፍ ብለው የማያርፉበት በረዷማ ምድር ላይ “ጽናት” መጽናት አቃታት። ዌድል ተብሎ በሚጠራው ባሕር ላይ በተንሳፈፈ ግግር በረዶ የተወሰኑ አስቼጋሪ ጊዜያትን ለማሳለፍ ተገደዱ። በቆይታቸው ሕይወታቸውን ለመታደግ ሲሉ ፒንጉዊን በመባል የሚጠሩ የዋልታ ወፎችን እና የባሕር አንበሳን እያደኑ መመገብ ግድ ነበር። ከዚህ የከፋው ግን ይዘዋቸው የሄዷቸውን ውሾች ሳይቀር እንዲመገቡ ተገድደው ነበር።
መርከባቸው ከግግሩ የማምለጥ ዕድል አልነበራትም መሰባበር እና መስጠም ጀመረች። ያኔ ለድንገተኛ አደጋ በሚል በትልልቅ መርከቦች ላይ የሚያዘውን ትንሽዬ ጀልባ ከመርከቧ አውርደው ለተወሰነ ጊዜ ሊቆዩ ወደሚችሉበት ኤለፋንት ደሴት ተሻገሩ።
በደሴቱ ብዙ የመቆየት ተስፋ እንደሌለ ያረጋገጠው ሻክልተን 5 አባላቱን ይዞ በትንሽዬዋ ጀልባ 800 ማይል ተጉዘው ጆርጂያ ደሴት ደረሱ።
ቀሪ 22 አባላቱን ለመታደግ የሚያስችለውን እርዳታ ለማግኘት አስቼጋሪውን ተራራማ ስፍራ ማቋረጥ ነበረባቸው። ወደ ደሴቷ ማዕከል ከገቡ በኋላ የእርዳታ መርከብ አመቻችተው ቀሪዎቹን አባላት ማምጣት ቻሉ።
የሰው ልጅ ተስፋ የሌለ በሚመስል ሁኔታ ውስጥ እንኳ ወድቆ ጽኑ ከኾነ ማለፍ የማይችለው ነገረ የለም። የሻክልተን ታሪክም ለዚህ ማረጋገጫ የሚኾን የጽናት እና አይበገሬነት ተምሳሌት ነው።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን