
ጎንደር፡ ሐምሌ 11/2017 ዓ.ም (አሚኮ)የጎንደር ዩንቨርሲቲ “ለሕይወት የተገናኙ፤ ለልህቀት የተዋሐዱ” በሚል መሪ መልዕክት ነው የቀድሞ ምሩቃን ቀንን እያከበረ የሚገኘው።
በመርሐ ግብሩ ላይ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት አስራት አጸደወይን (ዶ.ር) የቀድሞ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንቶች፣ ሠራተኞች፣ የቀድሞ ምሩቃን እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
በመርሐ ግብሩ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት አስራት አጸደወይን (ዶ.ር) የቀድሞ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ምሩቃን ሀገር እና ሕዝብን በቅንነት በማገልገል ትልቅ አሻራ ማስቀመጣቸውን አስረድተዋል።
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ መስከረም 1947 የመማር ማስተማር መጀመሩን የገለጹት ፕሬዝዳንቱ ዩኒቨርሲቲው ሰኔ 30/1949 ዓ.ም በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የጤና ባለሙያዎችን ማስመረቁን ገልጸዋል።
ዩኒቨርሲቲው ባለፉት ዓመታት ከ107ሺህ በላይ ተማሪዎችን ማስመረቁን የገለጹት ፕሬዝዳንቱ እነዚህን ምሩቃን ለማሰብ እና ለማስታወስ የቀድሞ ምሩቃን ቀን መዘጋጀቱን ተናግረዋል።
የቀድሞ ተማሪዎች ቀን የተማሪዎች የጋራ ዓላማ የሚታይበት፣ ትዝታቸውን ወደ ኃላ ተመልሰው የሚያስታውሱበት እና በቀጣይ ለዩኒቨርሲቲው ዕድገት የበኩላቸውን ጉልህ ድርሻ ለመወጣት ቃል ኪዳን የሚገቡበት ዕለት መኾኑንም ተናግረዋል።
የቀድሞ ተማሪዎች ኅብረትን በማቋቋም የካበተ ልምድ እና ዕውቀት ባለቤት የኾኑ የቀድሞ ተማሪዎች ሁሉ ለተቋሙ ሃብት የሚያፈላልጉበት፣ በጥናት እና ምርምር የሚሳተፉበት፣ ዩኒቨርሲቲውን በዓለም አቀፍ ደረጃ ለማስተዋወቅ በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲወጡ የሚያደርጉበት ሥራ ይሠራል ነው የተባለው።
በመርሐ ግብሩ ላይ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የቀድሞ ተማሪዎች ማኅበር እንደሚመሠረት፣ የማኅበሩ አርማ የሚተዋወቅበት ሥርዓት እውን እንደሚኾን፣ የጎንደር ዩንቨርሲቲ ምሩቃን መረጃ ማሠባሰቢያ ሥርዓት እንደሚሠራ ተመላክቷል።
ከዚህ በተጨማሪም የአርዓያ ሰብዕ እና የበጎ ተጽዕኖ ፈጣሪ ምሩቃን መታሰቢያ ገጽ በቅርቡ በይፋ ወደ ሥራ እንደሚገባ ፕሬዝዳንቱ ገልጸዋል።
ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ላለፉት 70 ዓመታት በመማር ማስተማር እና ላለፉት 100 ዓመታት ደግሞ በጤናው ዘርፍ ዘርፈ ብዙ አስተዋጽኦ ማበርከቱ በመርሐ ግብሩ ተነስቷል።
ዩኒቨርሲቲው ከጥር 13/2017 ዓ.ም ጀምሮ እያከበረ በሚገኘው የምስረታ በዓሉ ላይ የተለያዩ ሁነቶችን አስተናግዷል።
ዩኒቨርሲቲው የቀድሞ ተማሪዎችን ከማሰብ ባሻገር ሐምሌ 12/2017 ዓ.ም ከ2 ሺህ 500 በላይ ተማሪዎችን ያስመርቃል።
ዘጋቢ፦ ደስታ ካሣ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን