እርስዎ በዓመት ስንት ጊዜ ቅድመ ምርመራ ያደርጋሉ?

9

ባሕር ዳር: ሐምሌ 11/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ብዙዎችን ካላመመን በስተቀር ወደ ሕክምና ተቋማት አንሄድም። ሰው ሳያመው ወደ ሕክምና መሄድ ምን የሚሉት ሟርት ነው የሚሉም አሉ።

አንዳንድ ብልሆች ግን አስቀድመው ጤንነታቸውን በሕክምና ያረጋግጣሉ። ሙሉ ምርመራ በማድረግ የጤንነታቸውን ኹኔታ ይጠብቃሉ።

የሀገሬው ሰው “ታሞ ከመማቀቅ አስቀድሞ መጠንቀቅ” የሚል ወርቃማ አባባል አለው። ታሞ ላለመማቀቅ ደግሞ በጥንቃቄ ጉድለት ከሚመጡ በሽታዎች ራስን መጠበቅ እና ሕመም ከመሰማቱ አስቀድሞ በቂ ምርምራ ማድረግ ያስፈልጋል።

በአፊላስ ጠቅላላ ሆስፒታል የውስጥ ደዌ ስፔሻሊስት ዶክተር ልዑል ሰለሞን የቅድመ ምርመራ የሚባለው በሰዎች ላይ ሊከሰቱ የሚችሉ በሽታዎችን ምልክት ከማሳየታቸው አስቀድሞ በምርመራ በመለየት የሰዎችን የጤና ኹኔታ ማረጋገጥ ነው ይላሉ።

አጠቃላይ የጤና ምርምር በየትኛውም የዕድሜ እርከን ላይ ባሉ አዋቂዎች እንዲደረግ ይመከራል ብለዋል። እድሜያቸው ከ40 ዓመት በላይ ያሉ ሰዎች በዓመት አንድ ጊዜ አጠቃላይ ምርመራ እንዲያደርጉ ይመከራል።

ዕድሜያቸው ከ40 ዓመት በላይ የኾኑ እና ተጓዳኝ ችግር ያለባቸው ከኾኑ ደግሞ ከአንድ ዓመት ባጠረ ጊዜ አጠቃላይ ምርመራ እንዲያደርጉ ነው የሚመከረው።

ዕድሜያቸው ከ20ዎቹ እና በ30ዎቹ ውስጥ ያሉ አዋቂዎች ደግሞ ከሁለት ዓመታት እስከ አምስት ዓመታት ድረስ አጠቃላይ ምርመራ ቢያደርጉ ጥሩ እንደሚኾን ገልጸዋል።

አጠቃላይ ምርመራዎችን ማድረግ በየዕድሜ እርከኖች ላይ ሊከሰቱ የሚችሉ ሕመሞች ሥር ሰድደው ሌሎች ችግሮችን ከማምጣቸው በፊት ቀድሞ ለመለየት ያስችላሉ ብለዋል።

በሽታዎች ሥር ከሰደዱ በኋላ ወደ ሕክምና መምጣት በሰዎች ላይ የሚኖረው ሕመም እና የገንዘብ ወጪ ከፍተኛ እንደሚኾን ነው የተናገሩት። አጠቃላይ ምርመራ ማድረግ በሽታዎች እንዳይከሰቱ ቅድመ ጥንቃቄ ለማድረግ ያስችላል ነው ያሉት።

ማኅበረሰቡ አጠቃላይ ምርመራ የማድረግ ልምዱ አናሳ ነው ያሉት ዶክተሩ ይህም ሊኾን የሚችለው በአጠቃላይ ምርመራ ሊኖር የሚችልን ግንዛቤ ባለማወቅ ነው ብለዋል። የቅድመ ምርመራ የሚያደርጉ ወገኖች በርካታ ጥቅሞችን እያገኙ መኾኑንም ተናግረዋል።

የጤና ተቋማት ማኅበረሰቡ የቅድመ ምርመራ እንዲያደርግ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን መሥራት እንደሚጠበቅባቸው አንስተዋል። ቅድመ ምርመራ በሽታዎች ሥር እንዳይሰዱ ለማድረግ እና ከሕመም ስቃይ ለመዳን እንደሚያስችል ተናግረዋል።

ማኅበረሰቡ የቅድመ ምርመራ ልምዱን በማሳደግ ጤንነቱን መጠበቅ እንደሚገባውም ገልጸዋል። የጤና ባለሙያዎች የታመመን ሰው ከማከም ባሸገር በሽታን የመከላከል ሥራዎች እንሠራለን ያሉት ዶክተሩ ለጤንነት የተሻለ የሚኾነው የቅድመ ምርመራ በማድረግ ጥንቃቄ ማድረግ ነው ብለዋል።

በተለይ በገጠሪቱ ኢትዮጵያ የሚገኙ ወገኖች የቅድመ ምርመራ እንዲያደርጉ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች መሠራት እንዳለባቸው ተናግረዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleሀገራዊውን የምክክር ጉባኤ ለማካሄድ አስቻይ ኹኔታዎች እንዲፈጠሩ እየተሠራ ነው።
Next articleየደብረ ማርቆስ መንገድ ጥገና ዲስትሪክት በሁሉም የጥገና ዓይነቶች ሥራዎችን እያከናወነ.መኾኑን የኢትዮጵያ መንገዶች አሥተዳደር አስታወቀ።