
ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 11/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የዜጎቻቸው የአዕምሮ ዕድገት ላይ የሠሩ ሀገራት ሥልጣኔያቸውን ከፍ አድርገዋል። ከቀደሙት ሥልጣኔዎች ላይ አዳዲስ ሥልጣኔዎችን እየደረቡ ሄደዋል። የሥልጣኔ መሠረቱ ትምህርት እና ዕውቀት ነው።
የዜጎቻቸው የአዕምሮ ዕድገት ላይ ያልሠሩ ሀገራት በአንጻሩ ሥልጣኔን ማረጋገጥ ሲቸገሩ ይስታዋላሉ።
እጓለ ገብረዮሐንስ የከፍተኛ ትምህርት ዘይቤ በተሰኘው መጽሐፋቸው ትምህርት ቀላል ነገር አይደለም፤ ስለ ትምህርት ያለን አስተያየት ትክክለኛ ከኾነ ማናቸውም የሕይወት ችግሮች ሊፈቱ ይችላሉ፤ ሰው ከሙሉ የሰውነት ደረጃ የሚደርሰው በትምህርት ነው ይላሉ።
ሊቁ እጓለ ፈላስፋው ፕላቶን ጠቅሰው ሲጽፉ ሰው ትክክለኛውን ትምህርት ያገኘ እንደኾነ ለስላሳ እና ፈጣሪውን የሚመስል ፍጥረት ነው፤ ትምህርት ያላገኘ እንደኾነ ግን በምድር ላይ ካሉት አራዊት የባሰ ለመኾኑ ጥርጥር የሌለው ነገር ነው ብለዋል።
ትምህርት ምንግዜም በየትም ሀገር ቢኾን ከዘመን እና ከቦታ ጋር የተያያዘ ነው። በዓለም መጀመሪያ ወይም በሥልጣኔ ታሪክ መጀመሪያ ላይ አይደለንም። በዓለም መጨረሻም አይደለንም፤ በመካከል ላይ ነን።
በኋላችን ብዙ ዘመናት አልፈዋል በእነዚህ ዘመናት ውስጥ ሰዎች በብዙ ትግል ውስጥ ያስገኟቸው የሥልጣኔ ቅርሶች እንደቦታው እና እንደ ዘመኑ የተለያዩ ናቸው። የትምህርት ጠባይ ከእነዚህ የሥልጣኔ ቅርሶች ጋር የተያያዘ ስለኾነ ብዙውን ጊዜ በማንበብ የምናሳልፍ ከኾነ ከነበርንበት ዘመን ጋር አብረን መጓዝ እንችላለን ይላሉ ሊቁ።
ማንበብ ሙሉ ሰው ያደርጋል የሚባል የተለመደ እና የቆየ አባባል አለ። ሙሉዕነት አንጻራዊ ቢኾንም ማንበብ ምክንያታዊ እና መልካም ግንዛቤ ያለው ሰው ግን ያደርጋል።
ተቋማት ከሕዝብ አገልግሎታቸው ባሻገር ለማንበብ የሚሰጡት ትኩረት ምን ያክል ይኾን ? ምን ያክሎቹስ ለአዕምሮ ልማት አሰበው ቤተ መጻሕፍትን ገንብተው ይኾን? በርካታ ተቋማት ዘመናዊ የመመገቢያ ቦታዎችን ሲያዘጋጁ ይስተዋላል። ቁም ነገሩ በዚሁ ልክ ምን ያክሎቹስ ለቤተ መጻሕፍት አሰበው ገንብተው ይኾን የሚለው ጉዳይ ነው።
በዛሬው የአሚኮ ምልከታ ወደ ክልሉ ገንዘብ ቢሮ አቅንተናል። ይህ ተቋም ሠራተኞቹ በዕውቀት ታግዘው ሥራቸውን ይሠሩ ዘንድ የመጻሕፍት ቤት ገንብቷል። በዚሁ ቢሮ ውስጥ ያለው ቤተ መጽሐፍት የተሟላ አገልግሎት እንደሚሰጥም ተመልክተናል።
አሚኮ ምልከታ ባደረገበት ወቅት በመጽሐፍት ቤቱ ውስጥ ሲያነቡ ያገኘናቸው ሙሉነህ አመረ ቤተ መጻሕፍቱ በመቋቋሙ ለሠራተኞች ከሥራቸው ጋር በተገናኘ ብዙ ጠቀሜታ እንዳለው ነው የተናገሩት።
የመንግሥት ሠራተኞች በዕውቀት ታግዘው አገልጋይነታቸውን እንዲያሳድጉ እና ባልባሌ ነገር ጊዜያቸውን እንዳያባክኑ የቤተ መጻሕፍቱ መቋቋም ትልቅ ጥቅም እንዳለው ገልጸዋል።
በርካታ ተቋማት እንዲህ አይነት ዕድል አለማግኘታቸውን ተናግረዋል። ሌሎች ቢሮዎችም ከዚህ ተሞክሮ መውሰድ ይገባቸዋል ብለዋል።
የመጻሕፍቱ ቤቱ አስነባቢ ወይዘሮ ሙሉዓለም ስንታየሁ የቤተ መጻሕፍቱ መቋቋም እንደ አርዓያ የሚወሰድ መኾኑን ገልጸዋል።
ቤተ መጻሕፍቱ ለተቋሙ ሠራተኞች ብቻ ሳይኾን ሌሎችም አገልግሎት እንደሚሰጥ ተናግረዋል። ሌሎች ቢሮዎችም በዚህ ዙሪያ መሥራት እንደሚገባቸው ነው የጠቆሙት።
የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ የሕዝብ ግንኘነት ኀላፊ ጌታቸው ቢያዝን ማንበብ ለአዕምሮ ልማት እድገት መሠረታዊ ነገር ነው ይላሉ።
የሰዎችን ተግባር ፣ አስተሳሰብ እና አመለካከት የሚቀረጸው በትምህርት እንደኾነ የተናገሩት ኀላፊው ይህም በማንበብ የሚደረጅ እንደኾነ ጠቁመዋል።
ትምህርት ቢሮ ቤተ መጻሕፍትን በማዘጋጀት እና የዲጂታል ቤተ መጻሕፍትን በመጠቀም ሠራተኞች ከመደበኛ ሥራቸው በተጨማሪ ባሉበት ቦታ ኾነው ዕውቀታቸውን የሚያዳብሩበት፤ የተለያዩ ነገሮችን የሚያጣቅሱበት የዲጂታል ቤተ መጽሐፍት እንዳለው ተናግረዋል።
በቀጣይም ዘመኑን የዋጁ የትምህርት መጻሕፍትን በመግዛት ሞያተኞች ከወቅቱ ጋር አብረው እንዲሄዱ ለማድረግ እንደሚሠራ ነው የጠቆሙት።
አንድ ተቋም ለመዝናኛ ካፊ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚገነባው እና በግብዓትም እንደሚያደራጀው ሁሉ ለአዕምሮ ልማትም አስቦ ቤተ መጽሐፍትን ማቋቋም ይጠበቅበታል ብለዋል።
ትምህርት ቢሮ የሚሠራው ሥራ ጥሩ አርዓያ መኾን እንደሚችል የተናገሩት ኀላፊው ሌሎች መሥሪያ ቤቶችም ከዚህ ልምድ በመውሰድ ምቹ የቤተ መጻሕፍት አገልግሎት ከዲጂታላይዜሽን ጋር በማቀናጀት መጀመር እንዳለባቸው ገልጸዋል።
ዘጋቢ፦ ሰመሀል ፍስሀ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን