ትኩረት ያጣው የመተማ የቁም እንስሳት ማቆያ ወደ ሥራ እንዲገባ ተጠየቀ።

15

ገንዳውኃ: ሐምሌ 10/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የክልል፣ የዞን ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች እና የሀገር መከላከያ ከፍተኛ አዛዦች በምዕራብ ጎንደር ዞን የመተማ የእንስሳት ኳራንታይንን ምልከታ አድርገዋል።

በሀገር ደረጃ ካሉት ውስን የእንሰሳት ኳራንታይን ውስጥ አንዱ በምዕራብ ጎንደር ዞን የሚገኘው የመተማ የእንስሳት ኳራንታይን ነው። ኳራታይኑ ሥራ እንዲጀምር የሁሉንም ድጋፍ ይሻል።

የአማራ ክልል ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ኀላፊ አየለ አናውጤ (ዶ.ር) ኳራንታይኑ መገንባቱ ደረጃውን እና ጥራቱን የጠበቀ እንስሳት ወደ ውጭ ሀገራት ለመላክ እንደሚያስችል ጠቁመዋል። ለሀገሪቱ ትልቅ የገቢ ምንጭ ስለኾነ ኳራንታይኑን ቶሎ ሥራ ማስጀመር እንደሚገባም ተናግረዋል።

ኳራንታይኑ ወደ ሥራ እንዲገባ ድጋፍ እና ክትትል እንደሚደረግም ተናግረዋል።ማኅበረሰቡ የእንስሳት ማቆያውን በእኔ ባይነት ስሜት ሊጠብቀው እና ሊቆጣጠረው ይገባል ነው ያሉት።

የምዕራብ ጎንደር ዞን ዋና አሥተዳዳሪ ኢያሱ ይላቅ በፌዴራል መንግሥት የተገነባው የዞኑ የእንስሳት ኳራንታይን በሕገ ወጥ መንገድ ወደ ጎረቤት ሀገር ሱዳን የሚወጡ እንስሳትን በመከላከል ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንዳለው ተናግረዋል።

በአካባቢው ያሉ አርብቶ አደሮች ከዘርፉ እንዲጠቀሙ ለማስቻል የመተማ የቁም እንስሳት ማቆያ ማዕከል ትልቅ አቅም እንደኾነም አስረድተዋል።

በዞኑ ያሉ የቁም እንስሳትን ሙሉ በሙሉ ለመጠቀም ኳራንታይኑን ፈጥኖ ወደ ሥራ ለማስገባት ሁሉም አካል ርብርብ ሊያድርግ ይገባል ብለዋል።

የምዕራብ ጎንደር ዞን ንግድና ገበያ ልማት መምሪያ ኀላፊ ጌትነት በሊሁን የእንስሳት ኳራንታይኑ የዞኑን የልማት እንቅስቃሴ የሚያነቃቃ ነው ብለዋል። የእንስሳት ማቆያው ለወጣቶች የሥራ ዕድል የሚፈጥር መኾኑንም አመላክተዋል።

በኳራንታይኑ ላይ ዝርፊያ የሚፈጽሙ አካላት ላይ መንግሥት ሕጋዊ እርምጃ ሊወስድ ይገባል ነው ያሉት።

ኳራንታይኑ ሥራ እንዲጀምር በሚደረገው ጥረት ሁሉም ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን መወጣት እንዳለበት መልዕክት አስተላልፈዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleልጆች ክረምቱን እንዴት ያሳልፉ?
Next articleለአዕምሮ ልማት ምን ያክል እየተሠራ ነው?