ልጆች ክረምቱን እንዴት ያሳልፉ?

19

ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 10/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በኢትዮጵያ የዘመን አቆጣጠር አራት ወቅቶች አሉ። መኸር፣ በጋ፣ ጸደይ ወይም ደግሞ በልግ እና ክረምት።

ከሰኔ ወር አጋማሽ ጀምሮ ያለው ወቅት ደግሞ የክረምት ወቅት ነው። በዚህ ጊዜ የተማሪዎች የ10 ወር መደበኛ የትምህርት መርሐ ግብር ተጠናቅቆ ትምህርት ቤቶች ለጥቂት ወራት ዝግ ይኾናሉ።

👉ታዲያ በእነዚህ ጊዚያት ልጆች እንዴት ያሳልፉ?

ተማሪ ፍፁም አንሙት የባሕርዳር ከተማ ነዋሪ ነው። በ2018 የስደስተኛ ክፍል ተማሪ ነው። ክረምቱን እንዴት ልታሳልፈው አሰብክ? ብለን ጠይቀነው ሲመልስ ከዚህ በፊት የክረምት የእረፍት ጊዜን እንደሚያሳልፍበት ሁሉ ዘንድሮም ለመጭው የትምህርት ጊዜ የሚያግዙ የተለያዩ ጽሑፎችን እያነበበ፣ ዘመድ እየጠየቀ እና ቤተሰቦቹን ሥራ እያገዘ እንደሚያሳልፍ ነግሮናል።

ሌላኛዋ የባሕር ዳር ነዋሪ ተማሪ መራዊት አስማማው በ2017 ዓ.ም የሰባተኛ ክፍል ተማሪ ነበረች። ከፍተኛ ውጤት በማስመዝገብ እና አንደኛ ደረጃን በመያዝ ወደ ስምንተኛ ክፍል ተዛውራለች።

የክረምት የእረፍት ጊዜዋን ቤተሰቦቿ በሚሰጧት ሃሳብ መሠረት እንደምታሳልፍም ገልጻለች።

👉ወላጆችስ ስለልጆቻቸው የክረምት የእረፍት ጊዜ ምን ይላሉ?

የባሕርዳር ከተማ ነዋሪዋ ወይዘሮ ለምለም አወቀ የሦስት ልጆች እናት ናቸው። በእረፍት ጊዜያቸው ልጆቻቸው በቂ የጨዋታ ጊዜ እንዲኖራቸው እንደሚያደርጉ አብራርተዋል።

ልጆች የክረምት ጊዜን በአግባቡ እንዲያሳልፉ እንደሚመክሩም ተናግረዋል። ነገር ግን የግድ ይሄ ካልኾነ ብለው ጫና እንደማይፈጥሩም ጨምረዋል።

ከቴክኖሎጅው እንዳይርቁም ዩቲዩብ እና ቲክቶክ ላይ ልጆችን የተመለከቱ ቪዲዮዎች (ተንቀሳቃሽ ምስሎች) በማውረድ እንዲያዩ እንደሚያደርጉም ነው የጠቆሙት።

ስልክ ላይ ብዙ ጊዜ ሲያሳልፉ የሚፈጥረው አሉታዊ ነገር እንዳለ በመረዳታቸው በቻሉት መጠን ለመቆጣጠር እንደሚሞክሩም ነው የጠቆሙት።

ሌላኛው ሀሳብ የሰጡን የባሕር ዳር ነዋሪ አቶ በሪሁን ታረቀኝ ደግሞ የአምስት ልጆች አባት ናቸው። ልጆቻቸው ሳይጨነቁ የእረፍት ጊዜያቸውን እንደየፍላጎታቸው እንዲያሳልፋ ትምህርት እንደተዘጋ የመመካከር ልምድ አለን አሉን።

በስፖርታዊ እንቅስቃሴ፣ በሃይማኖታዊ ትምህርቶች እና በቋንቋ ሥልጠና እንደየፍላጎታቸው ጊዜያቸውን ያሳልፋሉም ብሏል።

👉ከእነዚህ ሀሳቦች በመነሳት ልጆች ከ10 ወራት የትምህርት ጊዜ በኋላ የክረምት የእረፍት ጊዜያቸውን እንዴት እና በምን ቢያሳልፉ የተሻለ ነው? ብለን ባለሙያ ጠይቀናል?

በባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ የሥነ ልቦና ትምህርት ክፍል መምህር፣ የአዕምሮ ጤና፣ የሥነ ልቦና እና ማኅበራዊ ድጋፍ ማኅበር ፕሬዝዳንት መሰረት አያሌው (ዶ.ር) በልጆች የክረምት የእረፍት ጊዜ ማሳለፊያ መንገዶች ላይ የተለያየ ዕይታ አለ አሉን።

ዶክተር መሠረት በፊት ይወጡ የነበሩ የጥናት ጹሑፎች እና ትንተናዎች ዕድሚያቸው እስከ 15 ዓመት የኾኑ ልጆች ቀድሞ የመገመት፣ ከሃይማኖት፣ ከማኅበራዊ እና ከፖለቲካዊ ኹኔታዎች አኳያ አዕምሯቸው ገና ያልዳበሩ ስለኾኑ መቆጣጠር ያስፈልጋቸዋል የሚል እንደኾነ ጠቁመዋል።

አሁን ላይ የሚወጡ ጥናቶች ግን በዋናነት ልጆች ያላቸውን ፍላጎት፣ ተሰጥኦ እና የቀጣይ ጉዟቸው ላይ መተኮር አለበት የሚል እንደኾነም አስረድተዋል፡፡

ከዚህ ጥናት በመነሳት የክረምት የእረፍት ጊዜ መልካም አጋጣሚ የሚፈጥር እንደኾነ ነው ያብራሩት፡፡ እረፍት በመውሰድ ወይም ደግሞ በመዝናናት እና ያላቸውን ክህሎት በመለየት ዝንባሌያቸውን እንዲያወጡ እድል መስጠት የተሻለ ነው አሉን።

ወላጆች የበለጠ ከልጆች ጋር ጊዜ የሚያሳልፉበትን እና የልጆችን ፍላጎት የሚለዩበት ጥሩ አጋጣሚ መኾኑንም ጠቁመዋል።

ልጆች የትኛውንም አይነት ጨዋታ መጫወት አለባቸው ያሉት ዶክተር መሠረት በጨዋታው ውስጥ ሲያስተባብሩ መሪነትን፣ እርስ በእርስ ሲጋጩ ችግርን በራስ መፍታትን፣ በጋራ የመኖር እና አብሮ የመሥራት ክህሎትን ብሎም የውድድር መንፈስን ይማራሉ እና የጨዋታ ጊዜንም ማሰብ መልካም ነው ብለዋል፡፡

ዶክተር መሠረት ጨምረውም የክረምት ጊዜ ለሚቀጥለው ዓመት ቅድመ ዝግጅት የሚያደርጉበት ጭምር ስለኾነ እንደዋናው ትምህርት ጊዜ በተጨናነቀ መንገድ ባይኾንም ልጆች ከጥናት እና ንባብ እንዳይርቁም መክረዋል።

👉በአብዛኛው ወላጆች ልጆቻቸው ክረምቱን የማጠናከሪያ ትምህርት በመማር እንዲያሳልፉ ይፈልጋሉ ተገቢ ነውን?

ዶክተር መሰረት ልጆች የክረምት የእረፍት ጊዜያቸው ትምህርት ላይ ከሚኾን ማንነታቸውን እንዲያውቁ፣ በራስ መተማመናቸው እንዲዳብር፣ ችግርን የመፍታት አቅማቸው እንዲያድግ የሚያደርጉ ተሰጥኦን የማጉላት እና የአዕምሮ ግንባታ ላይ የሚያተኩሩ ኹኔታዎች ላይ ቢያሳልፉ የተሻለ ለቀጣይ ህይወታቸው መሰረት እንደሚኾን ገልጸዋል።

ከቁጥጥር አኳያም ወላጆች ልጆች የእረፍት ጊዜ ላይ ናቸው በሚል ሙሉ በሙሉ መልቀቅ አይገባቸውም ብለዋል።

ዘጋቢ፦ ሮዛ የሻነህ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous article118 ፕሮጀክቶችን እየገነባ መኾኑን የምዕራብ ጎጃም ዞን እና አካበቢው አልማ ጽሕፈት አስታወቀ።
Next articleትኩረት ያጣው የመተማ የቁም እንስሳት ማቆያ ወደ ሥራ እንዲገባ ተጠየቀ።