
ሰቆጣ: ሐምሌ 10/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ጋዝጊብላ ወረዳ ዛሮታ ቀበሌ ሽምዝረይ ተፋሰስ “በመትከል ማንሰራራት” በሚል መሪ መልዕክት የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር ተካሂዷል።
የዛሮታ ቀበሌ ባለፉት አራት ዓመታት የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብርን በማካሄዳቸው አካባቢው አረንጓዴ እየለበሰ መምጣቱን ችግኝ ሲተክሉ ያገኘናቸው አቶ አስረሱ ተገይ ተናግረዋል። የተከሉትን ችግኝም ተንከባክበው ለማሳደግ ልዩ ምልክት እንዳደረጉ ጠቁመዋል።
ወይዘሮ መልካምአየሁ ካሴ የሽምዝረይ ተፋሰስ ደኑ ተራቁቶ እንደነበር ተናግረዋል። በየዓመቱ ችግኝ በመተከላቸው የዛሮታ ወንዝ እየጠነከረ እንዲመጣ አግዞታል ነው ያሉት። የተተከሉ ችግኞች እንዲያድጉ ማኅበረሰቡ መንከባከብ እና ከእንስሳት ንክኪ ተፋሰሱን ማጽዳት ይገባል ብለዋል።
የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ግብርና መምሪያ ምክትል ኀላፊ ሞገስ ኀይሌ በብሔረሰብ አሥተዳደሩ በሁሉም ወረዳዎች እና ከተማ መሥተዳድሮች ከ1 ሺህ 900 ሄክታር በላይ በሚኾን የተመረጠ ቦታ ላይ ከ4 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ ችግኝ እንደሚተከል ገልጸዋል።
የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር በሁሉም የዞኑ አካባቢዎች በተጠናከረ መንገድ ይቀጥላል ብለዋል።
ዋግ ኽምራን ከበረሃማነት የሚያወጣት ብቸኛው መንገድ የአረንጓዴ አሻራ መኾኑን የገለጹት ደግሞ በዛሮታ ቀበሌ ተገኝተው አሻራቸውን ያስቀመጡት የብሔረሰብ አሥተዳደሩ ዋና አሥተዳዳሪ ኀይሉ ግርማይ ናቸው። የሚተከሉ ችግኞች ለኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ የሚውሉ፣ ሀገር በቀል ተክሎች፣ ለውበት የሚኾኑ ችግኞችን ያካትታል ያሉት አሥተዳዳሪው “ችግኞቹን ተክለን የምንተዋቸው ሳይኾን እንደበኩር ልጅ የምንከባከባቸው ናቸው”ብለዋል።
ማኅበረሰቡ ችግኝ ለመትከል በኅብረት እንደዘመተው ሁሉ በኅብረት በመጠበቅ አካባቢውን ወደ ደኅንነት ለመቀየር በጋራ መሥራት እንደሚገባ አሳስበዋል።
ዘጋቢ:- ደጀን ታምሩ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!