
ፍኖተ ሰላም፡ ሐምሌ 10/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በተለያዩ የጤና ተቋማት የደም እጥረት የሚያጋጥማቸው ታካሚዎች በስፋት እየተስተዋለ ነው።
የምዕራብ ጎጃም ወጣቶች እና ስፖርት መምሪያ ከደብረ ማርቆስ ደም ባንክ አገልግሎት ጋር በመተባበር በክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የደም ልገሳ ፕሮግራም በፍኖተ ሰላም ከተማ አካሂዷል።
በደም ልገሳ መርሐግብሩ ላይም የመንግሥት ሠራተኞች፣ በጎ ፈቃደኞች እና የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል።
አሚኮ ያነጋገራቸው ደም ለጋሾችም ደም መለገስ በደም እጥረት ምክንያት እየተሰቃዩ ያሉ ታካሚዎችን ችግር የሚቀርፍ በመኾኑ የህሊና እርካታ እንደሚሰጣቸው ተናግረዋል።
የደም እጥረትን ከመቅረፍ ባለፈ የጤና ጥቅም እንደሚያስገኝላቸው ተረድተው ደም መለገሳቸውን ገልጸዋል። የሚተካ ደምን በመስጠት የማይተካ ሕይወትን መታደግ መኾኑንም አንስተዋል።
በአኹኑ ወቅት የደም እጥረት በመኖሩ በርካታ እናቶች፣ ሕጻናት እና ቀዶ ሕክምና የሚሰጣቸው ታካሚዎች አስቸጋሪ ኹኔታን እያሳለፉ መኾናቸውን በደብረ ማርቆስ ደም ባንክ አገልግሎት የጤና ባለሙያ ሲስተር እፀገነት ገብረማርያም ተናግረዋል።
ያለው የደም አቅርቦት እና ደም የሚያስፈልጋቸው ሕሙማን ባለመጣጣሙ ከፍተኛ ችግር እየተፈጠረ መኾኑን አብራርተዋል።
በመኾኑም ደም መለገስ ክቡር የኾነውን የሰው ሕይወት መታደግ ስለኾነ ሁሉም በዚህ ሰብዓዊነት ተግባር እንዲሳተፍ ጥሪ አቅርበዋል።
በምዕራብ ጎጃም ዞን በበጎ ፈቃድ አገልግሎት 2 ሺህ ዩኒት ደም ለመሠብሠብ እየተሠራ መኾኑን የዞኑ ወጣቶች እና ስፖርት መምሪያ ኀላፊ በውቀቱ ተሾመ ተናግረዋል።
በዚህም በጎ ፈቃደኞች እና የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች እንደሚሳተፉ ተገልጿል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን