
ደብረ ማርቆስ፡ ሐምሌ 10/2017 ዓ.ም (አሚኮ) 452 የንጹህ መጠጥ ውኃ ተቋማትን በመገንባት የዞኑን የንጹህ መጠጥ ውኃ ሽፋንን ወደ 48 ነጥብ 8 በመቶ ከፍ ማድረጉን የምሥራቅ ጎጃም ዞን ውኃ እና ኢነርጅ ልማት መምሪያ አስታውቋል፡፡
የምሥራቅ ጎጃም ዞን ውኃ እና ኢነርጅ ልማት መምሪያ ኀላፊ ፍሬው ካሴ በተጠናቀቀው የ2017 በጀት ዓመት ከ445 ሚሊዮን ብር በላይ በኾነ ወጭ 452 የንጹህ መጠጥ ውኃ ተቋማትን በመገንባት ኅብረተሰቡን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ገልጸዋል።
አነስተኛ እና መለስተኛ የውኃ ጉድጎዶች፣ የገመድ ፓምፕ፣ የምንጭ ማጎልበት እና ሌሎችንም ጨምሮ በአጠቃላይ 452 የንፁህ መጠጥ ውኃ ተቋማትን በመገንባት ከ180 ሺህ በላይ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል።
የንጹህ መጠጥ ውኃ ፕሮጀክቶች ከአሥተዳደር ምክር ቤቶች፣ ከረጂ ድርጅቶች፣ ከክልሉ መንግሥት በተገኘ የበጀት ድጋፍ እና በማኅበረሰቡ ተሳትፎ የተገነቡ መኾናቸውን መምሪያ ኀላፊው አመላክተዋል፡፡
በዚህ ዓመት የተገነቡትን ጨምሮ በዞኑ የሚገኙ ከ10 ሺህ በላይ የንጹህ መጠጥ ውኃ ተቋማት ከ1 ሚሊዮን በላይ የኅብተረሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ እያደረጉ ነው። ሽፋኑም 48 ነጥብ 8 በመቶ መድረሱን ነው ኀላፊው የተናገሩት፡፡
ኅብረተሰቡ የውኃ ተቋማትን የመገንባት ልምዱ እየተሻሻለ ነው ያሉት ኀላፊው በበጀት ዓመቱ 17 የንጹህ መጠጥ ውኃ ተቋማትን በራስ አቅም በመገንባት ጥቅም ላይ እንዲውሉ ስለማድረጉም ጠቁመዋል፡፡
የጮቄ የውኃ ማማን ጨምሮ ከ50 በላይ ወንዞች እና የ237 ምንጮች መገኛ የኾነው ምሥራቅ ጎጃም ዞን አኹንም በሚፈለገው ልክ የንጹህ መጠጥ ውኃ ተጠቃሚ ኾኗል ለማለት የማያስደፍር በመኾኑ በዘርፉ ላይ ሰፊ ሥራዎችን መሥራት እንደሚጠበቅ ኀላፊው አስገንዝበዋል፡፡
በዞኑ የጥናት እና ዲዛይን ሥራቸው ተጠናቅቆ ግንባታቸው ያልተጠናቀቁ 12 የውኃ ተቋማት እንደሚገኙም ገልጸዋል።
ኀላፊው የኅብተሰቡ የረጅም ጊዜ ጥያቄ የኾኑት የውኃ ተቋማት ፕሮጀክቶች ግንባታ ለማጠናቀቅ በ2018 በዕቅድ ተይዘው በልዩ ትኩረት እንደሚሠራ ነው ያመላከቱት፡፡
በ2018 በጀት ዓመት 760 የንጹህ መጠጥ ውኃ ፕሮጀክቶችን በመገንባት የዞኑን የንጹህ መጠጥ ውኃ ሽፋን ወደ 60 በመቶ ለማሳደግ ስለመታቀዱም ተመላክቷል፡፡
የኢነርጂ ዘርፉን በማነቃቃት የደን ምንጣሮን ለመቀነስ በተሠራው ሥራ በበጀት ዓመቱ ከ45 ሺህ በላይ ማገዶ ቆጣቢ ምድጃዎችን ጥቅም ላይ ማዋል መቻሉን አብራርተዋል።
137 ባዮጋዝ በማዘጋጀት ከ800 በላይ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉንም ነው ያስገነዘቡት፡፡
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን