
ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 10/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ሰላም እና ጸጥታ መምሪያ በ2017 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈጻጻም እና የክረምት ወራት ተግባራት ዙሪያ ውይይት አካሂዷል።
በመድረኩ የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው እና ሌሎችም የከተማ አሥተዳደሩ፣ የክፍለ ከተማ እና የቀበሌ የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል።
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው በበጀት ዓመቱ የከተማዋን ሰላም ማረጋገጥ የዓመቱ ቀዳሚ ተግባር በማድረግ በመሠራቱ የተሻለ ሰላም ማረጋገጥ ተችሏል ብለዋል።
የተቀናጀ የጸጥታ ሥራ በመሠራቱም የባሕር ዳር ከተማን ሰላም ማረጋገጥ እና ለጎብኝዎች ምቹ ማድረግ መቻሉን አመላክተዋል።
በከተማዋ ልማቶች እየተከናወኑ የሚገኙት የተሻለ ሰላም ስለመጣ ነው፤ አኹን ኹሉም የልማት ሥራዎች ያለምንም ችግር በታሰበው እና በታቀደው ልክ እየተሠሩ ነው ብለዋል።
በከተማዋ የሚገኙት አገልግሎት ሰጭ ተቋማት ትክክለኛ እና መደበኛ የሥራ ተግባራቸውን እያከናወኑ እንደሚገኙ አንስተዋል። በአሁኑ ወቅት በሰላም እጦት ምክንያት የሚስተጓጎል ምንም አይነት እንቅስቃሴ የለም ነው ያሉት።
ሕዝቡ ያለምንም ችግር ወጥቶ የሚገባበት እና ጎብኝዎችም ያለምንም ስጋት የሚጎበኟት ከተማ የማድረግ ሥራን አጠናክረው እንደሚቀጥሉም ነው ያስረዱት።
የከተማዋን ሰላም ለማሥቀጠል የጸጥታ መዋቅሩ ወንጀለኞችን መያዝ ብቻ ሳይኾን የወንጀል ምርመራ አቅምን በማሳደግ ለሕዝቡ ዋስተና መኾንን ለማረጋገጥ እንደሚሠራም አመላክተዋል።
ባሕር ዳር ከተማ በርካታ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ጎብኝዎችን የምታስተናግድ ከተማ መኾኗን የጠቀሱት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው አኹን ላይ ሰላም በመምጣቱ ጎብኝዎች መጥተው በሰላም የሚመለሱባት ኾናለች ነው ያሉት።
መላው ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያንም ከተማዋን እንዲጎበኙ እና ኢንቨስት እንዲያደርጉም ጥሪ አቅርበዋል።
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ሰላም እና ጸጥታ መምሪያ ኀላፊ ጌትነት አናጋው በበጀት ዓመቱ የከተማዋን የጸጥታ ኀይል በማደራጀት እና ሥምሪት በመስጠት ወደ ተግባር በመገባቱ በከተማዋ የተሻለ ሰላም ማምጣት ተችሏል ብለዋል።
በበጀት ዓመቱ በርካታ ሁነቶች የተከናወኑበት እና የልማት ፕሮጀክቶችም ያለምንም ችግር የተሠሩበት መኾኑ የሰላሙ ውጤት ማሳያ እንደኾነም አንስተዋል።
ይህንን ሰላም ለማስቀጠል እና ከክረምቱ ጋር ተያይዞ ሊፈጠሩ የሚችሉ ወንጀሎችን ለይቶ ለመቆጣጠር የሚያስችል ዕቅድ በማቀድ ለጸጥታ መዋቅሩ ስምሪት ተሰጥቶ እየተሠራ መኾኑንም ተናግረዋል።
የ9ኛ ፖሊስ ጣቢያ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ኢንስፔክተር ደመቀ አስማረ የጸጥታ መዋቅሩም ከሰላም ወዳዱ ማኅበረሰብ ጋር በመኾን በቅንጅት እየሠራ መኾኑን ገልጸዋል።
ማኅበረሰቡ የጸጥታው ባለቤት ኾኖ ወንጀለኞችን በመጠቆም እና በመያዝ ከጸጥታ መዋቅሩ ጎን ኾኖ እያገዘ እንደሚገኝ ተናግረዋል። በዚህም የወንጀል ድርጊቶችን መቀነስ መቻሉን እና የተሻለ ሰላም መምጣቱን አመላክተዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን