የተተከሉ ችግኞች እንዲጸድቁ አስፈላጊው ክትትል ይደረጋል።

6

ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 10/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ሠራተኞች በባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር በፋሲሎ እና መስከረም 16 ትምህርት ቤቶች ችግኝ ተክለዋል።

በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የማኅበራዊ ዘርፍ አስተባባሪ እና የትምህርት ቢሮ ኀላፊ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ.ር) እና ሌሎች የቢሮው ከፍተኛ መሪዎች ተሳትፈዋል።

በችግኝ ተከላው የተሳተፉት የቢሮው ሠራተኛ ህብስቴ ካሴ ለበጋው የትምህርት ጊዜ ቅድመ ዝግጅት ከሚደረግባቸው ሥራዎች መካከል ትምህርት ቤቶችን ሳቢ ማድረግ ነው ብለዋል። ለዚህም ችግኝ መትከል አንዱ መኾኑን አንስተዋል።

የሚተከሉት ችግኞች ግቢውን ማሳመር ብቻ ሳይኾን ለምግብነት እንዲኹም ለጥላነት የሚያገለግሉ እንደኾኑ ገልጸዋል።

ትምህርት ቢሮው በትምህርት ቤቶች ችግኞች መተከላቸውን እና እንዲጸድቁም ባሉት አደረጃጀቶች ድጋፍ እና ክትትል እንደሚያደርጉ ወይዘሮ ህብስቴ ገልጸዋል።

ሌላኛው የችግኝ ተከላው ተሳታፊ ባለሙያ ጌታነህ መንግሥት የአረንጓዴ አሻራን በትምህርት ቤቶች ማሳረፍ የአየር ንብረት ሚዛንን ከመጠበቅ በተጨማሪ የትምህርት ቤቶችን ገጽታም እንደሚገነባ ተናግረዋል።

የተተከሉት የአፕል እና ማንጎ ዝርያ ችግኞች ለትምህርት ቤት ምገባም አስተዋጽኦ እንደሚኖራቸው ገልጸዋል።

ችግኞቹ እንዲጸድቁ በየትምህርት ቤቶቹ ባሉት የአካባቢ ጥበቃ ክበብ አማካይነት እንክብካቤ ይደረጋል ነው ያሉት አቶ ጌታነህ።

በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የማኅበራዊ ዘርፍ አስተባባሪ እና የትምህርት ቢሮ ኀላፊ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ.ር) የትምህርት ተቋም አንዱ ሥራ ችግኝ መትከል መኾኑን ገልጸዋል።

የተተከሉት ችግኞች ለምግብነት የሚያገለግሉ እና ሥነ ምህዳርን የሚጠብቁ መኾናቸውን የጠቆሙት ዶክተር ሙሉነሽ እንዲጸድቁም አስፈላጊውን ክትትል እና ድጋፍ ይደረጋል ብለዋል።

ለምግብነት የሚውሉ ችግኞችን መትከል ሁሉም እንዲንከባከባቸው እንደሚያደርግ ያነሱት ዶክተር ሙሉነሽ በአዲሱ ሥርዓተ ትምህርት የሥራ እና ተግባር ትምህርትን በግብርናው ዘርፍ ላይ ለመተግበርም ምቹ መኾኑን ተናግረዋል።

ችግኝ ስንተክል ጥላቻ እና ጠብን ነቅለን ሰላም እና ፍቅርን እንትከል ብለን እየሠራን ነው።

ለቀጣይ የመማር ማስተማር ሰላማዊነት በክረምቱ ሰላም እና ፍቅርን ጨምረን መትከል እና ማረጋገጥ አለብን ነው ያሉት ዶክተር ሙሉነሽ።

ዘጋቢ፦ ዋሴ ባዬ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleምክር ቤቱ የተሻሻለውን የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ እና የምርጫ ሥነ ምግባር አዋጅ አጸደቀ።
Next articleየባሕር ዳር ከተማን ሰላም ማረጋገጥ እና ለጎብኝዎች ምቹ ማድረግ ተችሏል።