
ሰቆጣ: ሐምሌ 10/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ጋዝጊብላ ወረዳ ዛሮታ ቀበሌ “ሽምዝረይ ተፋሰስ” የአረንጓዴ አሻራ የማስጀመሪያ መርሐ ግብር እየተካሄደ ነው።
በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ከ4 ነጥብ 5 ሚሊዮን ችግኝ ለመትከል ታቅዶ እየተሠራ ነው። የማስጀመሪያ መርሐ ግብሩም የክልል እና የዞን መሪዎች በተገኙበት ተጀምሯል።
የጋዝጊብላ ወረዳ ዋና አሥተዳዳሪ አበባው ደሳለኝ በአካባቢው ያለውን ሰላም በማጽናት የአረንጓዴ አሻራን ለመትከል በነቂስ እየተንቀሳቀሱ መኾኑን ነው የተናገሩት።
በወረዳው በ21 ቀበሌዎች በ31 ለተከላ የተለዩ ቦታዎች ላይ በ436 ነጥብ 5 ሄክታር መሬት ላይ ከ870 ሺህ በላይ የደን ችግኝ እና 25 ሺህ ቋሚ የኢኮኖሚ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞችን ለመትከል መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።
የአካባቢው ማኅበረሰብም ችግኝ ከመትከል ባለፈ በመንከባከብ እና በመጠበቅ በኩል የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ አሳስበዋል።
በዛሮታ ቀበሌ ተገኝተው አሻራቸውን ያስቀመጡት የአማራ ክልል ሲቢል ሰርቢስ ኮሚሽን አማካሪ ተፈራ ካሳ በዋግ ኽምራ ተገኝተው የአረንጓዴ አሻራ በማስቀመጣቸው የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል።
ዋግ ኽምራ የተራቆተ እና ተደጋጋሚ ድርቅ የሚከሰትበት ከባቢ በመኾኑ የአረንጓዴ አሻራን መትከል ለዋግ ሕዝብ የውዴታ ግዴታ መኾን አለበት ብለዋል።
የአካባቢው ማኅበረሰብም ችግኝ ከመትከል ባሻገር መንከባከብ እንደሚገባ አቶ ተፈራ ካሳ አሳስበዋል።
በአረንጓዴ አሻራ በማስጀመሪያ መርሐ ግብር ላይ የመንግሥት ከፍተኛ መሪዎች እና የተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል።
ዘጋቢ:- ደጀን ታምሩ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!