
ባሕር ዳር: ሐምሌ 10/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ዲጂታል ሥርዓት በኮምፒውተር እና የዲጂታል ቴክኖሎጂ በመታገዝ ግልጽነትን በማስፈን፣ ብክነትን፣ ድካምን እና ጊዜን በመቆጠብ የምጣኔ ሀብት እድገትን ያፋጥናል። የዜጎችንም ሕይወት ያቀልላል፡፡ ኋላቀር በኾነ አሠራር የተጓተተ፣ ጥራት የሌለው እና ዜጎች ርካታ ያጡበት የነበረን ሥርዓት ወደ ምርታማ እና ስኬታማ መንገድ ይቀይራል፡፡
ኢትዮጵያም የአምስት ዓመት ዲጂታል ስትራቴጂ ነድፋ ሊታይ የሚችል ፍሬ ማፍራት ጀምራለች፡፡ ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ የአምስት ዓመት ቆይታውን ሊደፍን ከወር ያነሰ ጊዜ ብቻ ይቀረዋል፡፡ ይህን ተከትሎም የ2030 ስትራቴጂ በዝግጅት ላይ ይገኛል፡፡
ስትራቴጂው የዲጂታል መሠረተ ልማትን በመዘርጋት ምጣኔ ሀብታዊ፣ ማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ እድገትን በኢትዮጵያ እንዲመጣ በማለም ነው ወደ ሥራ እንዲገባ የተደረገው፡፡
ኢትዮጵያን በዲጂታል ቴክኖሎጂ ከፍ ለማድረግ እና የሕዝቧንም ሕይወት ቀላል፣ ቀልጣፋ እና ከብክነት የሚጠብቅ ለማድረግ የተዘጋጀ መኾኑን የነገሩን በኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የዲጂታል ኢኮኖሚ ልማት ሥራ አስፈጻሚ ስዩም መንገሻ ስትራቴጂው አድራሽ ተብለው በተለዩ መንገዶች እና መሠረቶች ላይ የተመረኮዘ እንደኾነ ገልጸዋል፡፡
አድራሽ መንገዶች የሚባሉት በሀገሪቱ ምጣኔ ሀብት ትልቅ ድርሻ ያላቸውን ግብርና፣ ማኑፋክቼሪንግ፣ ቱሪዝም እና የመረጃ ቴክኖሎጂን ያቀፉ ናቸው። እነዚህን ወደ መሬት አውርዶ በዲጂታል ሥርዓት ለማዘመን ዋልታ ኾነው የሚያገለግሉት ደግሞ መሠረቶች ይባላሉ ነው ያሉት።
የዲጂታል ሥነ ምኅዳር፣ ኤሌክትሮኒክስ የመንግሥት አገልግሎት እና ንግድ የመሳሰሉ ዲጂታል መደላድሎች (ፕላትፎርምስ) እና አስቻይ ሥርዓትን መፍጠር ለስትራቴጂው መሰረቶች ናቸውም ብለዋል፡፡
መሪ ሥራ አስፈጻሚው ዓለም ከደረሰበት የዲጂታል በረከት ሀገራችንም ተቋዳሽ እንድትኾን ስትራቴጂው አጋዥ እንደኾነም አስረድተዋል፡፡ በኢቲዮ ቴሌኮም የለውጥ ሥራ (ሪፎርም) የግል ኩባንያዎች መግባት ያመጣውን የተደራሽነት እድገት፣ በሰዎች ዘንድ ቅቡልነቱ እያደገ የመጣውን የዲጂታል ግብይት አማራጭ መጎልበት፣ ወደ ዲጂታል ሥርዓት እየመጣ ያለው የመንግሥት አገልግሎት እና የማንነት መለያ የኾነው የፋይዳ መታወቂያ መጀመር ስትራቴጂውን ተከትለው የታዩ ፍሬዎች መኾናቸውን ጠቁመዋል፡፡
በሀገሪቱ እስከ አሁን ከ900 በላይ የመንግሥት ተቋማት አገልግሎቶቻቸውን በመስመር (ኦንላይን) ማድረጋቸው ሕይወት ማቅለሉን ገልጸዋል። ከዚህ በፊት ጊዜን፣ ገንዘብን እና ጉልበትን ያባክን የነበረው የመንግሥት የግዥ ሥርዓት ዲጂታል መኾኑ የስትራቴጂው ውጤት መኾኑን ተናግረዋል።
ዲጂታል ሥርዓት መዘርጋት ብቻውን ግብ አይደለም፡፡ ነገር ግን ያንን በመጠቀም ሥራን የሚያሳልጥ በቴክኖሎጂ ክህሎቱን እና ዕውቀቱን ያዳበረ ዜጋ ያስፈልጋል፡፡ በመኾኑም ዘርፉ ትኩረት ተሰጥቶት ሥራዎች እየተሠሩ ናቸው፡፡
ስትራቴጂው ስኬታማ እንዲኾን ኢትዮጵያ ከተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ጋር በመተባበር ለ5 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን ከክፍያ ነፃ ዓለም አቀፍ የዲጂታል ቴክኖሎጂ ሥልጠና ተመቻችቶ ዜጎች የዲጂታል ቴክኖሎጂ ክህሎት እና ዕውቀት እያገኙ መኾኑን ተናግረዋል። ሥልጠናው አሁንም ክፍት እንደኾነ እና በተቋም ደረጃም የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር በርካታ የግንዛቤ ፈጠራ ሥራዎችን መሥራቱን ገልጸዋል፡፡
የዲጂታል ሥርዓትን ማስፈን እና ለማኅበረሰቡ ግልጽ፣ ቀላል እና ተደራሽ የኾነ አገልግሎት ማድረስ የስትራቴጂው መዳረሻ ነው፡፡
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!