
ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 09/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያ ውስጥ ሰላም እንዲሰፍን የተለያዩ አካላት በተደጋጋሚ ጥሪ ሲያቀርቡ ይሰማል፡፡
በአማራ ክልል የሰላም ሁኔታው እየተሻሻለ ቢኾንም ሰላሙ አስተማማኝ ደረጃ እንዲደርስ ከሚጠይቁት አካላት አንዱ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ነው፡፡
የአማራ ክልል የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ የክልሉን ሰላም ለማረጋገጥ በሚሠሩ ሥራዎች ላይ ከሁሉም ቤተ እምነት የሃይማኖት አባቶችን ያካተተ ሀገር አቀፍ የሰላም ጉባኤ ከሰኔ 4/2017 ዓ.ም እስከ ሰኔ 5/2017 ዓ.ም ማካሄዱ ይታወሳል፡፡
በኮንፈረንሱ ከተለያዩ ሚዲያዎች፣ ከክልሎች የተውጣጡ የሃይማኖት አባቶች፣ የመንግሥት አካላት በየድርሻቸው የሰላምን ዋጋ እንዲገልጡ የተደረገበት እና ሌሎች ክልሎችም ይህንኑ ተሞክሮ የወሰዱበት እንደነበር ተገልጿል።
ይህ የሰላም ኮንፈረስ በ2018 ዓ.ም በሁሉም ክልል እና ዞኖች መካሄድ እንዳለበት በመታመኑ የቅድመ ዝግጅት ሥራ እየተሠራ መኾኑን በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የባሕርዳር ሀገረ ስብከት ዋና ጸሐፊ እና የአማራ ክልል የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ አባል መልአከ ብርሃን ፍስሃ ጥላሁን ተናግረዋል፡፡
በንግግር ብቻ ሳይኾን እስከ ታች በመውረድ ሥራ መሥራት ይገባል ያሉት መልአከ ብርሃን ፍስሃ ጥላሁን ችግሮቻችን በሰላም እንፍታ፣ ወንድም ወንድሙን አይግደል፣ በመገዳደል ሰላምን ማምጣት አይቻልም፣ በመገዳደል የክልሉንም ኾነ የሀገርን ጥያቄ መፍታት አይቻልም፣ በእርስ በእርስ ጦርነት ማንም አሸናፊ አይኾንም የሚለውን ሀሳብ በግጭት ላይ ያሉ ሰዎችንም ኾነ ማኅበረሰቡን ለማሳመን ሰፊ ንቅናቄ እየተደረገ ነው ብለዋል።
ሰላም እንኳንስ ለሰው ልጅ በምድሪቱ ላሉ ፍጥረታት ያስፈልጋል ነው ያሉት፡፡ በሰሜኑ ጦርነት እጽዋቶች ሁሉ ነደዋል፣ አዝርእቶች ከምድረ ገጽ ጠፍተዋል፣እንስሳት በያሉበት ወድቀዋል፣ ስለዚህ የሃይማኖት አባቶች ቅድሚያ ለአምላካቸው ጸሎት ማድረግ ይገባቸዋል ብለዋል።
ከሚመለከተው አካል ጋርም በመወያየት ወደ ሰላም ለመምጣት ጥረት ማድረግ ይገባል ነው ያሉት፡፡
ማኅበረሰቡም የሚጠፋውን እና በጎውን ነገር እንዲለይ የግንዛቤ ፈጠራ ሥራ መሥራት ከሃይማኖት ተቋማት እንደሚጠበቅ አስገንዝበዋል፡፡
የአማራ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት የትምህርት እና የደዓዋ ዘርፍ ኀላፊ ሼህ ሙሐመድ ኢብራሂም ሰላም እንዲመጣ፣ መተሳሰብ እንዲኖር፣ መረዳዳት እንዲመጣ፣ የነበረው ችግር ቆሞ አብሮነት እንዲቀጥል የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ከዚህ በፊት ሦሥት የሰላም ኮንፈረንስ ማድረጉን አስገንዝበዋል፡፡
በቀጣይም በሁሉም ክልሎች ኮንፈረንሱ ይቀጥላል ነው ያሉት። በዚህም ሰላም እንዲመጣ ማኅበረሰቡን በማስተማር የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ ይሠራል ብለዋል።
በመስጊዶች የሰላም መልዕክቶች በየጊዜው እየተላለፉ መኾናቸውን ተናግረዋል።
ሰላም አቻ የለሽ፣ በዋጋ የማይለካ፣ መኾኑ ታውቆ ሁሉም ሰው ሰላም ለማምጣት መረባረብ እንዳለበትም አንስተዋል።
እንደ ሀገር ተሰሚነት አላቸው የሚባሉ የሃይማት አባቶች በመኾናቸው የሰላም መገለጫ መኾን ይገባቸዋል፣ ለቤተሰቦቻቸው እና ለልጆቻቸው ሰላም መንገር ይጠበቅባቸዋል ነው ያሉት።
ማኅበረሰቡም የሃይማኖት አባቶች የሚናገሩትን የሰላም ጥሪ በመቀበል የሰላም ተባባሪ ሊኾን ይገባል ብለዋል፡፡
ዘጋቢ፦ ሰናይት በየነ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን