
ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 09/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በባሕር ዳር ከተማ የሚገኙ አረጋውያን ማኅበር፣ እድር እና ጀሚያዎች ኅብረት በባሕር ዳር ዲፖ አዲሱ የመዝናኛ ስፍራ የችግኝ ተከላ አካሂደዋል፡፡
ከጀሚያ ቶፊቅ የእድር ማኅበር የመጡት አቶ ከድር አድኖ ችግኝ ሲተክሉ ነው አሚኮ ያገኛቸው፡፡ ለአራት ዓመታት በችግኝ ተከላ መሳተፋቸውን ነግረውናል፡፡
ችግኝ መትከል አካባቢን በመጠበቅ ለቀጣዩ ትውልድ ማስረከብ ነው ብለዋል፡፡
ከአሁን በፊት ከመትከል ባለፈ እንክብካቤ ላይ ውስንነት መኖሩን ገልጸዋል። ዛሬ የተከሏቸውን ችግኞች በቀጣይ ተንከባክበው እንዲጸድቁ ለማድረግ እንደሚሠሩ ተናግረዋል።
ሌላው ችግኝ ሲተክሉ አሚኮ ያገኛቸው የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር የዕድሮች እና የጀሚያ ጥምረት ኮሚቴ አባል አቶ ዮሃንስ መኮንን ችግኞች ቅርሶች ናቸው፣ እኛም እንደ አባትነታችን አሻራችን አሳርፈናል ብለዋል፡፡
ችግኞች እንዲጸድቁ በተተከሉበት ቦታ ባለቤት ኖሯቸው እንክብካቤ እንዲደረግ እና በራሳቸው አቅምም እንደሚንከባከቡ ተናግረዋል፡፡
ከዚህ በፊት የመንግሥት ሠራተኛ በነበሩበት ጊዜ ችግኞችን ይተክሉ እንደነበር ያስታወሱት አቶ ዮሃንስ ከተከሉ በኋላ ወደ ቦታው ሄደው ለመንከባከብ ጊዜ አለመስጠታቸውን ነው የገለጹት፡፡
ችግኝ መትከል ለከተማ ውበት፣ ለመዝናኛ እና ለአካባቢ ጥበቃ ያለውን ጥቅም ተረድቶ ከመትከል ባለፈ ትኩረት ሰጥቶ መንከባከብ አስፈላጊ ነው ብለዋል፡፡
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር አረጋውያን ማኅበር ሠብሣቢ መቶ አለቃ ሲሳይ ብርሃኑ በማኅበሩ ስም የችግኝ ተከላ በመካሄዱ ደስተኛ መኾናቸውን ገልጸዋል፡፡
ችግኞችን መትከል ብቻ ሳይኾን ተንከባክበን ለልጆቻችን እናስረክባለን ነው ያሉት፡፡ የአረጋውያን ማኅበር ከእድሮች እና የጀሚያ ማኅበር ጋር በጋራ ኾነው በራሳቸው ወጭ ችግኞችን ገዝተው በዲፖ መዝናኛ ሥፍራ ላይ መትከላቸውን ተናግረዋል፡፡
ከአሁን በፊት በድባንቄ ተራራ ችግኝ እንደተከሉ የተናገሩት ሠብሣቢው አረጋውያን ለብቻቸው የተለየ ቦታ ተሰጥቷቸው ሲተክሉ ግን የመጀመሪያቸው መኾኑን ነው የገለጹት፡፡
ከአሁን በፊት የተተከሉት ላይ የእንክብካቤ ሥራ አልሠራንም፣ አሁን ግን የተከልነውን ችግኝ ለመንከባከብ ዝግጁ ነን ነው ያሉት፡፡
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር የሴቶች፣ ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ መምሪያ ኀላፊ ሰብለ ዘውዱ የችግኝ ተከላውን ያካሄዱት የአረጋውያን ማኅበር፣ የእድር እና የጀሚያዎች ጥምረት በራሳቸው ተነሳሽነት ለችግኝ 75ሺህ ብር ወጭ አድርገው አሻራቸውን አሳርፈዋል ነው ያሉት፡፡
ችግኝ መትከል በኅብረት የሚሠራ በመኾኑ ይህም አንድነትን የሚጠናክር፣ ለትውልዱ በሁሉም ዘርፎች ነገን የሚስተካከል፣ የባሕር ዳር ከተማ ሙቀት እና የአካባቢን አየር ንብረት ለመጠበቅ የሚረዳ መኾኑን ገልጸዋል።
ከአሁን ቀደም የተተከሉ ችግኞችን መንከባከብ ላይ ውስንነት እንደነበር አንስተዋል። ችግኞችን በቅርብ በሚያገኙበት ቦታ የተከሉ በመኾኑ መትከል ብቻ ሳይኾን በባለቤትነት ስሜት የመንከባከቡ ሥራ ተኩረት ተሰጥቶ ሊሠራ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
ዘጋቢ፡ ፍሬሕይወት አዘዘው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን