
ሰቆጣ፡ ሐምሌ 09/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በዋግ ኽምራ ያለውን አንጻራዊ ሰላም የበለጠ ለማጽናት እየተሠራ ይገኛል። ሰላም ወዳዱ የዋግ ኽምራ ሕዝብም ከመንግሥትና ከሰላም ጎን መቆሙን በሰላማዊ ሰልፍ ድጋፍ ጭምር አሳይቷል።
ይህንን ሰላም አጽንቶ ለመጠበቅና የተረጋጋ አካባቢን ለመፍጠር ሕዝቡ ከመሪዎቹ ጎን ተሰልፎ እየሠራ እንደሚገኝ በብልጽግና ፓርቲ የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የፖለቲካ ዘርፍ ኀላፊ ሔኖክ ነጋሽ ገልጸዋል።
መሪዎች እስከ ቀበሌ ድረስ በመውረድ ለሰላም መጽናት የሚከፍሉት ዋጋ ከፍተኛ መኾኑንም ጠቅሰዋል።
የዋግ ኽምራን የመልማት ጥያቄ መፍታት የሚቻለው ሰላምን መጠበቅ ሲቻል ነው ያሉት ደግሞ የብሔረሰብ አሥተዳደሩ መሬት መምሪያ ኀላፊ ሚሰው ፈንታየ ናቸው።
ሕዝቡ በሰላማዊ ሰልፍ ወጥቶ ለሰላም ያለውን ቁርጠኛነት ሲረጋግጥ ከመሪዎችም የሕዝቡን ፍላጎት በመመልከት በጥበብ መምራትና የልማቱ ተጠቃሚ ለማድረግ በትጋት መሥራት ይጠበቃል ነው ያሉት።
የሰቆጣ ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጌትነት እሸቱ ከፊታችን የሚከበረውን የሻደይ በዓል በሰላም ለማክበር ከባለድርሻ አካላት ጋር የጋራ ውይይት መደረጉን ተናግረዋል።
ከሕዝቡ ጋር በተደረጉ የውይይት መድረኮችም ማኅበረሰቡ ሰላም እንዲኖር አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጧል ነው ያሉት።
የብሔረሰብ አሥተዳደሩ ሰላምና ጸጥታ መምሪያ ኃላፊ ሃምሳ አለቃ አዘዘው አዳነ በዋግ ኽምራ ሁሉም አካባቢዎች አንጻራዊ ሰላም ቢኖርም በአጎራባች ዞኖች የሚንቀሳቀሰው የጽንፈኛ ቡድን ማኅበረሰቡ ተንቀሳቅሶ እንዳይሠራ እንቅፋት መኾኑን ተናግረዋል።
በዞኑ ያለው ሰላም የተገኘውም ወጣቶች ከጸጥታ መዋቅሩ፣ ከመሪዎች እና ከማኅበረሰቡ ጋር በቅንጅት በመሥራታቸው መኾኑን ያስታወሱት ኃላፊው በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት ዋግ ኽምራ አካባቢ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ከ500 በላይ ታጣቂ ኃይሎች ለሰላም እጅ ሰጥተው ከማኅበረሰቡ ጋር እየኖሩ መኾኑን አንስተዋል።
ለሰላም ቀኑ መሽቶ አያቅምና አኹንም የታጠቁ ኃይሎች በማይጠቅም ጦርነት ሕዝባቸውን እና ራሳውን ከመጉዳት ወጥተው ለሰላም እጅ ሰጥተው ችግሮችን በውይይት እንዲፈቱ መምሪያ ኀላፊው ጥሪ አቅርበዋል።
ዘጋቢ፦ ደጀን ታምሩ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!