የሥነ ልቦና ጉዳት እና መፍትሔው፦

    116

    ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 09/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ሥነ ልቦና ስለ ሰዎች ስሜት፣ ባህርይ እና አስተሳሰብ የሚያጠና የትምህርት ዘርፍ ነው። አንድ ሰው በአካል፣ በመንፈስ እና በስሜት መልካም መስተጋብር ላይ ሲኾን የሥነ ልቦና ደኅንነት ላይ ነው ይባላል።

    አንድ ሰው በተለያዩ ምክንያቶች ከጤናማ አመለካከት፣ አስተሳሰብ እና ስሜት መስተጋብር ሲወጣ ደግሞ የሥነ ልቦና ችግር ላይ እንደኾነ ነው ባለሙያዎቹ የሚገልጹት።

    ሰዎች በተለያየ መንገድ ለሥነ ልቦና ችግር ሊጋለጡ ይችላሉ። አጋላጭ ከኾኑ ምክንያቶች ውስጥ ጦርነት አንዱ ነው። ሕጻናት እና ሴቶች ደግሞ ይበልጥ የችግሩ ሰለባ ሲኾኑ ይስተዋላሉ።

    በጦርነቱ የአካላዊ እና የሥነ ልቦና ተጋላጭ ከኾኑት ውስጥ በአጋር ኢትዮጵያ የሴቶች መጠለያ ማዕከል ያገኘናት ተጎጅ ትገኝበታለች።

    ተጎጅዋ በምትኖርበት አካባቢ በተከሰተው ጦርነት ሰብአዊ እና ቁሳዊ ጉዳት ሲደርስ ተመልክታለች። በእግሯ ላይም በጥይት ጉዳት ደርሶባታል።

    የወላጆቿ በሕይወት አለመኖር፣ በወቅቱ አጋዥ የነበረችው አክስቷ በጤና እክል ምክንያት አልጋ ላይ ከመኾኗ ጋር ተደማምሮ ተስፋ መቆረጥ ውስጥ እንደነበረች ነግራናለች።

    ይኹን እንጅ ወደ ማዕከሉ የመቀላቀል ዕድሉን ካገኘችበት ጊዜ ጀምሮ በወቅቱ ከነበረው የተስፋ መቁረጥ ስሜት በመውጣት ነገን በአዲስ የመኖር ተስፋ ማየት ጀምራለች።

    በአጋር ኢትዮጵያ የሴቶች መጠለያ ማዕከል የምክር ባለሙያ ሜሮን መስፍን የተለያዩ አካላዊ እና ሥነ ልቦናዊ ጉዳት የደረሰባቸው ሴቶች እና ሕጻናት መጠለያን ጨምሮ የምግብ እና የአልባሳት ድጋፍ ያገኛሉ።

    የሥነ ልቦና፣ የጤና እና የሕግ አገልግሎት እንዲኹም የተለያዩ ሥልጠናዎችን እንዲያገኙ እየተደረገ መኾኑንም ገልጸዋል። በሴቶች ላይ የሚደርሰው ጉዳት ተደራራቢ በመኾኑ ትኩረት እንዲሰጠውም ጠይቀዋል።

    የአማራ ክልል ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በንብረት ዝርፊያ፣ ጠለፋ እና ሰውን ማፈን እና ራስን ማጥፋት ላይ ጥናቶችን አድርጎ ነበር።

    ጥናቱ ባሕር ዳር፣ ጎንደር፣ ደብረ ማቆስ፣ ደብረ ብርሃን እና ደሴ ከተሞች ላይ ያተኮረ ነው። በጥናቱ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ተካትተዋል።

    በዚህም በክልሉ የተፈጠረውን የጸጥታ ሁኔታ በመጠቀም ጠለፋ፣ ዝርፊያ እና ሰውን አስገድዶ ማፈን ባልተለመደ ኹኔታ እየጨመረ መምጣቱን መግለጹ ይታወሳል።

    ራስን ማጥፋት በክልሉ መጨመሩን ነው ኢንስቲትዩቱ ይፋ ያደረገው። ለዚህ ደግሞ የአእምሮ ጤና ወታወክ ዋነኛው ምክንያት ኾኖ ተቀምጧል። ጾታዊ ጥቃት፣ ጠለፋ፣ ዝርፊያ እና የቤተሰብ ግንኙነት ችግር ራስን ለማጥፋት ሌላኛው ምክንያት መኾኑን ነው የተገለጸው።

    የችግሩ ተጠቂ ከኾኑት ውስጥ ደግሞ ከ11 እስከ 29 ዓመት የእድሜ ክልል የሚገኙ ወጣቶች 78 በመቶ የሚኾነውን ድርሻው እንደሚወስዱ ገልጸዋል።

    በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የሶሻልወርክ መምህርት እና ተመራማሪ ሰብለወንጌል አይናለም (ዶ.ር) የሥነ ልቦና ችግር በአብዛኛው በጦርነት፣ በንብረት ውድመት፣ በመፈናቀል፣ በስደት፣ በቤተሰብ ግጭት፣ በድኅነት፣ በሥራ ጫና፣ ጤናማ ባልኾነ የሥራ አካባቢ ምክንያት ሊከሰት ይችላል።

    የስሜት አለመረጋጋት፣ ከሰዎች ጋር መጋጨት፣ ራስን እና ሌሎች ሰዎችን የመጉዳት ፍላጎት ደግሞ ከሚታዩ ምልክቶች ውስጥ ይጠቀሳሉ።

    የንግግር መዛባት፣ ሰዎች ያሳድዱኛል ብሎ ማሰብ፣ ቅዠት፣ እንቅልፍ ማጣት፣ ምንም ሳይሠሩ የድካም ስሜትም ሊያስከትል ይችላል። ሰዎችን መጠራጠር፣ ፍርሃት፣ ራስን ከሰዎች ማግለል፣ ጥልቅ ድብርት ውስጥ መግባት ብሎም የአእምሮ መታመም ሌሎች ችግሮች ናቸው።

    ተመራማሪዋ እንዳሉት እንደ ሀገር ለሥነ ልቦና የተሰጠው ትኩረት ዝቅተኛ ነው። በኅበረተሰቡ ዘንድ የሚታይበት መንገድም የተዛባ መኾኑን ነው የገለጹት።

    ሰዎች የሥነ ልቦና ችግር ምልክቶችን እያሳዩ እና ችግራቸውን እየተናገሩ እንኳ ትኩረት ሰለማያገኙ ብዙዎች ለጉዳት መዳረጋቸውን ገልጸዋል።

    ችግሩን እንደ ሕመም ያለመቁጠር ይባስ ብሎ የፈጣሪ ቁጣ ተደርጎ እንደሚቆጠር ነው ያስገነዘቡት። ይህ ደግሞ በሀገሪቱ የተጠናከረ የሥነ ልቦና ተቋማት ካለመኖር እና ከባለሙያ እጥረት ጋር ተያይዞ ችግሩ ውስብስብ እንዲኾን ማድረጉን ገልጸዋል።

    በግጭት ወቅትም ኾነ በማንኛውም ምክንያት የሥነ ልቦና ጉዳት ያጋጠመውን ሰው ከችግሩ እንዲወጣ የሚያግዙ መፍትሔዎችንም መምህርት እና ተመራማሪ ሰብለወንጌል አሥቀምጠዋል።

    በግጭት ወቅት ሊያጋጥም የሚችለውን ደም መፍሰስ ለማቆም እና ሊደርስ የሚችለውን ስቃይ ለመቀነስ የመጀመሪያ ደረጃ እርዳታ እንደ ሚሠጠው ሁሉ በሥነ ልቦና ችግር ውስጥ የሚገኙ ሰዎችን ለማረጋጋት የመጀመሪያ ደረጃ የሥነ ልቦና ድጋፍ መስጠት አይነተኛው መንገድ መኾኑን ገልጸዋል።

    የመጀመሪያ ደረጃ የሥነ ልቦና ድጋፍ አገልግሎት ተደራሽነትን ከማስፋት አኳያ ፋይዳው የጎላ በመኾኑ ተማሪዎችን፣ ቤተሰብን እና በማኅበረሰቡ ውስጥ የሚገኙ አደረጃጀቶችን ማሠልጠን ይገባል ብለዋል።

    ውስብስብ የኾኑ የሥነ ልቦና ችግሮችን ለመፍታት በተለይም ደግሞ “ትራውማ ኢንፎርምድ ኬር እና ክሊኒካል ስፔሻላይዝድ ኬር” የሥነ ልቦና አገልግሎት መስጫ አማራጭን ማስፋት ይገባል ነው ያሉት።

    ለዚህ ደግሞ የሥነ ልቦና ትምህርትን በትምህርት ቤት እና በዩኒቨርሲቲዎች በተደራጀ መንገድ በመስጠት የሠለጠኑ ባለሙያዎችን ማፍራት ላይ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት እንደሚገባ መክረዋል።

    አገልግሎቱ ሳይንሳዊ ዘዴን ተከትሎ የሚሰጥ የሥነ ልቦና አገልግሎት በመኾኑ ከችግሩ ለመውጣት አይነተኛ መፍትሔ መኾኑንም አንስተዋል።

    ከጤና ተቋማት ባለፈ በትምህርት ተቋማት፣ በሆስፒታሎች፣ በሕግ እና ሌሎች ተቋማት አካባቢ የሠለጠኑ ባለሙያዎችን በመመደብ አገልግሎት መሥጠትም እንደሚያስፈልግ ነው የገለጹት።

    ማኅበረሰብ አቀፍ የሥነ ልቦና አገልግሎት መሥጫ ተቋማትን ማስፋት ሌላኛው አማራጭ ሊኾን እንደሚገባ አንስተዋል።

    በኢትዮጵያ ያለው ማኅበራዊ ትስስር ጠንካራ በመኾኑ ለሃይማኖት አባቶች፣ ለሀገር ሽማግሌዎች፣ ለታዋቂ እናቶች መሠረታዊ የሥነ ልቦና ድጋፍ ሥልጠና በመሥጠት ከዚህ በፊት በተለምዶ ይሰጡት የነበረውን ምክር በተደራጀ መንገድ አገልግሎቱን እንዲሠጡ ያግዛል ብለዋል።

    የአማራ ክልል ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩትም እየደረሰ ላለው የሥነ ልቦና ጉዳት የመፍትሄ ሃሳብ ጠቁሟል። የሥነ አእምሮ ችግር ያለባቸውን ሰዎችን ፈጥኖ ወደ ጤና ተቋማት ማድረስ፣ አምራች እና ጤናማ ትውልድ ለመፍጠር የስፖርት ማዘውተሪያ ቦታዎችን ማስፋፋት እና ለወጣቱ የሥራ እድል መፍጠር ላይ እንደመፍትሔ አስቀምጧል።

    የጤና ተቋማት እና ጤና ላይ የሚሠሩ ድርጅቶች፣ ከፍተኛ የትምህርት እና የሃይማኖት ተቋማትም የሥነ አእምሮ እና የሥነ ልቦና ትምህርት ሊሠጡ እንደሚገባ ጠቁሟል።

    ዘጋቢ ፦ ዳግማዊ ተሠራ

    የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

    https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
    ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

    Previous articleበአረንጓዴ አሻራ መርሐግብር የተከሏቸውን ችግኞች እንደሚንከባከቡ በደቡብ ወሎ ዞን የአርጎባ ብሔረሰብ ልዩ ወረዳ ነዋሪዎች ተናገሩ።
    Next articleየተረጋጋ ሰላም እንዲኖር መሪዎች እና ሕዝቡ በቅንጅት እየሠሩ ነው።