
ባሕር ዳር: ሐምሌ 09/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል እና የአፋር ክልሎችን የሚያገናኘው ይህ የመንገድ ፕሮጀክት 74 ነጥብ 3 ኪሎ ሜትር ይሸፍናል። መንገዱ በአስፋልት ኮንክሪት ደረጃ በመገንባት ላይ እንደሚገኝም የኢትዮጵያ መንገዶች አሥተዳደር አስታውቋል። አሁን ላይ የግንባታው አጠቃላይ አፈጻጸም 40 ነጥብ 95 በመቶ ደርሷል። የአፈጻጸም ሂደቱን ይበልጥ አጠናክሮ ለማስቀጠል በትኩረት እየተሠራ ይገኛል ተብሏል።
በእስካሁኑ የግንባታ ሥራዎች መካከል የጠረጋ፣ የአፈር ቁፋሮ፣ የአፈር ሙሌት፣ የማፋሰሻ ቱቦ፣ የተለያዩ የተፋሰስ ሥራዎች በመከናወን ላይ ናቸው። የሁለት ድልድይ፣ የአነስተኛ እና ከፍተኛ ከልቨርቶች ሥራም የግንባታው አካል መኾናቸውን ተገልጿል። በተጨማሪም የአስፋልት ንጣፍ ሥራ ለማስጀመር የሚረዱ አስፈላጊ ጥረቶች በመደረግ ላይ ናቸው ተብሏል።
አሁንም ድረስ ያልተፈቱ የወሰን ማስከበር ሥራዎች፣ አልፎ አልፎ የሚከሰቱ የጸጥታ ችግሮች እና የግብዓት እጥረቶች የፕሮጀክቱ ፈተና ናቸው ብሏል አሥተዳደሩ። ያጋጠሙ ችግሮች በሚፈቱበት ሁኔታ ላይ የተቀናጀ ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝም አመላክቷል። የመንገድ ግንባታውን ሀገር በቀሎቹ ፓወርኮን ኮንስትራክሽን ከአሰር ኮንስትራክሽን ጋር በመተባበር ያከናውኑታል። የፕሮጀክቱን ጥራት እና ቁጥጥር ኮር ኮንሰልቲንግ ያከናውናል። ለፕሮጀክቱ 2 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር ተመድቧል። ወጪው በፌደራል መንግሥት በጀት ይሸፈናል።
ነባሩ መንገድ ከ4 እስከ 7 ሜትር ያልበለጠ የጎን ስፋት የነበረው እና በአገልግሎት ብዛት የተጎዳ በመኾኑ ለተጠቃሚው ምቹ አልነበረም። አሁን ላይ ግንባታው ደረጃውን ጠብቆ እየተከናወነ ነው። ሲጠናቀቅ ከሐይቅ ተነስቶ ጭፍራ ከተማ ለመጓዝ ቀድሞ ይፈጅ የነበረውን 3:00 የጉዞ ጊዜ ወደ 1:00 ያሳጥረዋል ነው የተባለው። በፕሮጀክቱ ክልል የሚገኙ በርካታ ከተሞችን በማስተሳሰር ማኅበራዊ እና ምጣኔ ሀብታዊ ዕድገትን ያጠናክራልም ተብሏል። ከኢትዮጵያ መንገዶች አሥተዳደር የተገኘው መረጃ እንደሚያመላክተው መንገዱ ሲጠናቀቅ የተለያዩ ምርት ውጤቶች በቀላሉ በማጓጓዝ የንግድ እንቅስቃሴውን ያቀላጥፋል ተብሏል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!