
ደባርቅ፡ ሐምሌ 08/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በ2017 ዓ.ም የዜጎች የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ከ600 ሺህ በላይ ዜጎችን ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሠራ እንደሚገኝ የሰሜን ጎንደር ዞን ወጣት እና ስፖርት መምሪያ ገልጿል። በበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ የሴቶችን ተሳትፎ እና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየተሠራ ነው ተብሏል።
የዜጎችን የእርስ በእርስ ግንኙነት እና ማኅበራዊ መስተጋብር ከሚያሳድጉ ጉዳዮች መካከል የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት አንዱ ነው።
የሰሜን ጎንደር ዞን ወጣት እና ስፖርት መምሪያ ኀላፊ መዝናናት ጣዕመ በሰሜን ጎንደር ዞን በዘንድሮው ዓመት በሚካሄደው የዜጎች የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ከ312 ሺህ በላይ ዜጎች ይሳተፋሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ገልጸዋል።
ከተሳታፊዎቹ መካከልም ከ200 ሺህ በላይ የሚኾኑት ወጣቶች እንደኾኑ ተናግረዋል፡፡
በክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት የአረንጓዴ አሻራ፣ የአቅመ ደካሞች ቤት ጥገና፣ የደም ልገሳ እና ሌሎችም ተግባራት እንደሚከናወኑ አብራርተዋል፡፡
በዞኑ ከ528 በላይ ዜጎችን በአዲስ ቤት ሥራ እና በጥገና ሥራ ተጠቃሚ ለማድረግ ታቅዷልም ብለዋል።
በጤና ዘርፍ ከሚሠሩ የበጎ ፈቃድ ተግባራት መካከል የሚጋጥሙ የደም እጥረቶችን ለመቅረፍም ከ400 ዩኒት በላይ ደም ለመሠብሠብ ታቅዶ ወደ ሥራ ተገብቷል ነው ያሉት።
በበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ ከ600 ሺህ በላይ የኅብረተሰብ ክፍሎች ተጠቃሚ እንደሚኾኑ የገለጹት ኀላፊዋ በዚህም ከ130 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ ለማዳን መታቀዱንም አብራርተዋል።
የደባርቅ ከተማ ወጣት እና ስፖርት ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ስጦታው ታጀበ ዕቅዶችን በማዘጋጀት እና የተለያዩ የንቅናቄ መድረኮችን በመፍጠር የግንዛቤ ፈጠራ ሥራ ሲሠራ ቆይቷል ብለዋል።
በከተማ አሥተዳደሩ በዘንድሮው ዓመት የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ከ30 ሺህ በላይ ዜጎች እንደሚሳተፉም ገልጸዋል።
ከ200 ሺህ በላይ የማኅበረሰብ ክፍሎችን በልዩ ልዩ ዘርፎች ተጠቃሚ ለማድረግ እንደሚሠራም አብራርተዋል።
በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር የበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ ከ16 ሺህ በላይ ችግኞች እንዲተከሉ ማድረግ መቻሉንም አንስተዋል።
በአካባቢው እየተከሰተ የሚገኘው የጸጥታ ችግር የበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ በታሰበለት የጊዜ ቅደም ተከተል እንዳይከናዎን እክል መፍጠሩንም አብራርተዋል።
በቀጣይም ችግሮችን በመለየት እና በመፍታት የማኅበረሰቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ተግባራትን ለማከናዎን እንደሚሠራም ተገልጿል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን