ውሾችን ለሚያሳብድ በሽታ የቅድመ መከላከል ክትባት በመስጠት የማኅበረሰቡን ጤንነት መጠበቅ ይገባል።

10

ገንዳውኃ: ሐምሌ 08/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የምዕራብ ጎንደር ዞን ለውሾች የቅድመ መከላከል ክትባት በመስጠት የማኅበረሰቡን ጤንነት ከተላላፊ ውሻን የሚያሳብድ በሽታ መጠበቅ እንደሚገባ የዞኑ እንስሳትና ዓሳ ሀብት ልማት ተጠሪ ጽሕፈት ቤት አስታውቋል።

በበጀት ዓመቱ ከ9 ሺህ በላይ ውሾችን ለመከተብ አቅዶ ወደ ሥራ መግባቱን የዞኑ እንስሳትና ዓሳ ሃብት ልማት ተጠሪ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ደሳለኝ ሞገስ ተናግረዋል። ክትባቱ በዞኑ ባሉ 63 የክትባት መስጫ ጣቢያዎች እንደሚሰጥም አሳውቀዋል።

ውሻን የሚያሳብድ በሽታ (Rabies) በአብዛኛው የሚከሰተው መስከረም ወር ላይ እንደኾነ ኀላፊው ገልጸው ይህን በሽታም ለመከላከል የቅድመ መከላከል ክትባት ከግንቦት ወር ጀምሮ እየተሰጠ እንደኾነም አስረድተዋል።

ማኅበረሰቡም ውሻው ከድሮው የተለየ ፀባይ ሲያሳይ በአቅራቢያው በሚገኝ የክትባት መስጫ ጣቢያ በመውሰድ ማስከተብ እንዳለበት አስገንዝበዋል። ባለፈው ዓመትም፣ በዚህ ዓመት ክትባቱን በበቂ ሁኔታ ተደራሽ ለማድረግ የጸጥታ ችግር እንቅፋት እንደኾነባቸውም ተናግረዋል።

ከጤና ተቋማት ጋር በመነጋገር የጋራ የኾነ ሥራ በመሥራት ክትባቱን እንዳስጀመሩም ተናግረዋል። በቫይረሱ ከተያዘው ውሻ ጤነኛው ውሻ እንዳይገናኝ ማሰር እንደሚገባ እና ሁሉም ማኅበረሰብ እንዲያስከትብም ኀላፊው ጥሪ አቅርበዋል።

የቋራ ወረዳ እንስሳት እና ዓሳ ሀብት ልማት ተጠሪ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ስንዴው አሕመድ
በከተማው ይህን አስከፊ በሽታ ለመከላከል ለመጀመሪያ ጊዜ በገለጉ ከተማ የክትባት አገልግሎት መስጠት መጀመሩን ገልጸዋል። እስካሁን ባለው ሂደት ከ120 በላይ ውሾች እንደተከተቡ ኀላፊው ተናግረዋል።

ለቫይረሱ እጅግ በጣም ተጋላጭ ከኾኑ እንስሳት መካከል ውሻ፣ ቀበሮ፣ ድመት፣ ተኩላ እና የሌሊት ወፍ መኾናቸውን ጠቅሰዋል። በከተማው በየትኛውም አቅጣጫ በየቤታቸው ኾነ በየአካባቢያቸው ያሉ ውሻዎችን ማኅበረሰቡ በሽታው ከመከሰቱ በፊት ማስከተብ እንዳለበት ኀላፊው አሳስበዋል።

አቶ ማንደፍሮ ወርቄ የገለጉ ከተማ አካባቢ ቀበሌ ነዋሪ ሲኾኑ ውሻን ለሚያሳብድ በሽታ ክትባት መምጣቱ ለማኅበረሰቡ ጠቃሚ ነው ብለዋል። በዚህ በሽታ በየዓመቱ ይቸገሩ እንደነበርም ተናግረዋል። አሁን ግን የዚህ ቅድመ መከላከል ክትባት በመምጣቱ ጭንቀታችንን ቀንሶልናል ብለዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleበኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር ከሰላም ማስከበር ጎን ለጎን በርካታ ፕሮጀክቶች ተገንብተዋል።
Next articleበሰሜን ጎንደር ዞን በበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ የሴቶችን ተሳትፎ እና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየተሠራ ነው።