በኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር ከሰላም ማስከበር ጎን ለጎን በርካታ ፕሮጀክቶች ተገንብተዋል።

12

ከሚሴ: ሐምሌ 08/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የብሔረሰብ ምክር ቤቱ 5ኛ ዙር 25ኛ መደበኛ ጉባኤውን አካሂዷል።
በጉባኤ በ2017 በጀት ዓመት የተሠሩ የሰላም፣ የልማትና የመልካም አሥተዳደር ሥራዎች ተገምግመዋል።

የብሔረሰብ አሥተዳደሩ ምክር ቤት አባል ክቡር ሲራጅ ጀማል በ2017 በጀት ዓመት በብሔረሰብ አሥተዳደሩ የቁጭት እቅድ በማቀድ ሰላምን ለማስፈን የተሠራው ሥራ አመርቂ ውጤት ማስመዝገቡን ገልጸዋል።

ብሔረሰብ አሥተዳደሩ ባደረገው የሰላም ጥሪ በርካታ ቁጥር ያላቸው ታጣቂዎች ወደ ሰላም እንዲመጡ መደረጉ በአካባቢው ሰላም እንዲሰፍን ማስቻሉን ጠቁመዋል።

ሌላዋ የምክር ቤቱ አባል ክብርት አሚናት ሁሴን በ2017 በጀት ዓመት በብሔረሰብ አሥተዳደሩ የሕዝብን የልማት ጥያቄዎች ለመመለስ በተደረገው ጥረት ከሰላሙ ጎን ለጎን በርካታ ፕሮጀክቶች መገንባታቸውን ጠቅሰዋል።

የኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር ምክር ቤት አፈጉባኤ ክብርት ፋጡማ ሞላ በ2017 በጀት ዓመት በብሔረሰብ አሥተዳደሩ ሰላምን ለማረጋገጥ በብሔረሰብ አሥተዳደሩ እና ከአጎራባች ዞኖች ጋር የጋራ የሰላም ፎረሞች መካሄዳቸውን አንስተዋል።

የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቱን ለማጠናከርም የተሠራው ሥራ አመርቂ ውጤት አስመዝግቧል ብለዋል።

የሚገነቡ መሠረተ ልማቶች በጥራትና በተያዘላቸው ጊዜ እንዲጠናቀቁ ምክር ቤቱ በቋሚ ኮሚቴዎች በኩል ክትትል እና ድጋፍ ሲያደርግ እንደነበረም አብራርተዋል።

በበጀት ዓመቱ የተመዘገቡ ውጤቶችን በማስቀጠል የነበሩ ክፍተቶችን በ2018 በጀት ዓመት ለመሙላት በምክር ቤቱ መግባባት ተፈጥሯል ብለዋል።

የኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር ዋና አሥተዳዳሪ አሕመድ አሊ በብሔረሰብ አሥተዳደሩ በ2017 በጀት ዓመት በተላለፈው የሰላም ጥሪ ከ750 በላይ ታጥቀው ሲንቀሳቀሱ የነበሩ አካላት ወደ ሰላም እንዲመጡ መደረጉንም አስረድተዋል።

ከአጎራባች ወረዳና ዞኖች ጋር ያለውን የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ለማጠናከር በጋራ በርካታ መድረኮችን በመፍጠርና የሰላም ኮሚቴዎችን በማቋቋም የተሠራው ሥራ በቀጠናው ሰላም እንዲሰፍን ማድረጉንም ዋና አሥተዳዳሪው ጠቁመዋል።

በ2017 በጀት ዓመት የሕዝብን የልማት ጥያቄዎች ለመፍታት በተሠራው ሥራ በብሔረሰብ አሥተዳደሩ ከ2 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር በላይ በኾነ ወጭ ከ223 በላይ ፕሮጀክቶቸ ተገንብተው መጠናቀቃቸውን ገልጸዋል።

በቀጣይም የሕዝብን የልማትና የመልካም አሥተዳደር ጥያቄዎች ለመፍታት የብሔረሰብ አሥተዳደሩ በትኩረት ይሠራልም ብለዋል ዋና አሥተዳዳሪው።

ዘጋቢ:- ይማም ኢብራሒም

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleስለ ከውል ውጭ የጉዳት ካሳ ምን ያውቃሉ?
Next articleውሾችን ለሚያሳብድ በሽታ የቅድመ መከላከል ክትባት በመስጠት የማኅበረሰቡን ጤንነት መጠበቅ ይገባል።