ስለ ከውል ውጭ የጉዳት ካሳ ምን ያውቃሉ?

10

ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 07/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ሰዎች በአንድም ኾነ በሌላ ምክንያት ጉዳት ሊደርስባቸው ይችላል፡፡ የጉዳቶቹ ምንጮች የወንጀል ድርጊቶች፣ በውል አለመፈጸም ወይም ከውል ውጪ በሚደርስ ኀላፊነት ሊኾኑ ይችላሉ።

በአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን የሕግ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ከፍተኛ የሕግ ባለሙያ ደመቀ ይብሬ ከውል ውጪ በሚደርስ ጉዳት ሕግ ዋነኛ ዓላማ ጉዳት ያደረሰውን አካል የሚለይ ሥርዓት በመዘርጋት የተጎዳን ሰው ተገቢውን ካሳ እንዲያገኝ ማድረግ እና ሌሎች ትምህርት እንዲወስዱ ማስቻል ነው ይላሉ።

ጉዳት የሚለው ቃል በፍትሐ ብሔር ሕጉ ትርጉም ያልተሰጠው ቢኾንም ከድንጋጌዎቹ አጠቃላይ ይዘት በመነሳት በሰው ጥቅም፣ አካል ወይም ሕይወት ላይ የሚደርስ ጉድለት መኾኑን መረዳት ይቻላል ይላሉ፡፡

በከውል ውጪ ኃላፊነት ሕግ መመሰረት ካሳ ለማስከፈል ተጎጂው ጉዳት የደረሰበት መኾኑን እና ጉዳቱም የደረሰው ኃላፊነት አለበት በሚባለው ሰው ድርጊት ወይም እሱ ኀላፊነት በሚወስድባቸው ድርጊቶች የደረሰ መኾኑን ማረጋገጥ እንዳለበትም አስገንዝበዋል፡፡

ከፍተኛ የሕግ ባለሙያው ከውል ውጭ የሚደርስ ኀላፊነት ሕግ መሰረት (የፍትሐ ብሔር ሕግ ቁጥር 2027) ሦስት ዓይነት የኃላፊነት ምንጮች እንዳሉ ይጠቅሳሉ እነሱም በጥፋት ላይ የተመሰረተ ኀላፊነት፣ ጥፋት ሳይኖር ኀላፊነት እና ሌላ ሰው ለሚያደርሰው ጉዳት የሚኖር ኃላፊነት ናቸው ይላሉ፡፡

የተለያዩ የጉዳት ዓይነቶች እንዳሉ የነገሩን ከፍተኛ የሕግ ባለሙያው አንደኛው ግልጽ የኾኑ ጉዳቶች ናቸው ብለዋል።

ግልጽ የኾኑ ጉዳቶች የሚባሉት የተጎጂውን ንብረት ወይም ገንዘብ ነክ ጥቅም በቀጥታ የሚነኩ ጉዳቶች ሲኾኑ ይህ የጉዳት ዓይነት አንድም በቀጥታ ንብረት ላይ የሚደርስ ጉዳትን አለያም በአካል ወይም በሕይወት ላይ የደረሰ ጉዳትን የሚያጠቃልል ነው ይላሉ፡፡

ግልጽ የኾኑ ጉዳቶች አኹን የደረሱ ወይም ወደፊት የሚደርሱ ጉዳቶች ሊኾኑ ይችላሉ የሚሉት ከፍተኛ የሕግ ባለሙያው የፍትሐ ብሔር ሕግ ቁጥር 2090 እንደሚያመለክተው አኹን ላይ በእርግጠኝነት የደረሱ እና በግልጽ የሚታወቁ ጉዳቶች ኾነው ጉዳቶቹ ከደረሱበት ጊዜ ጀምሮ የጉዳት እና የካሳ መጠኑ በፍርድ ቤት እስከ ሚወሰን ድረስ ያለውን ጊዜ የሚመለከት ነው ብለዋል፡፡

ወደፊት የሚደርስጉዳትን በተመለከተ ከፍተኛ የሕግ ባለሙያው የፍትሐ ብሔር ሕግ ቁጥር. 2092 እንደሚያስረዳው በደረሰው ጉዳት እና በካሳ ተመኑ ላይ ፍርድ ከተሰጠ በኋላ ጉዳቶቹ የማይቆሙ እና የሚቀጥሉ የጉዳት ዓይነቶች እንደኾኑ ያትታል፡፡

ሌላው የጉዳት አይነት የህሊና ጉዳት ነው። የህሊና ጉዳት የተጎጂውን የኢኮኖሚ ነክ ጥቅሞችን የሚጎዳ ሳይኾን በተጎጂው ላይ የስሜት መጎዳት፣ ሀዘን፣ ሀፍረትን የመሳሰሉ ሞራላዊ የኾኑ ጉዳቶችን የሚፈጥር የጉዳት ዓይነት ስለመኾኑም ዘርዝረዋል፡፡

ጉዳትን ተከትሎ የሚመጣው የጉዳት ካሳ ሲኾን ይህም ጉዳቱ ለደረሰበት ሰው የጉዳት መጠኑ ተሰልቶ በዛ ልክ የሚሰጠው ጥቅም ስለመኾኑ የፍትሐ ብሔር ሕግ ቁጥር 2090(1), 2091 ያስረዳል፡፡

ለተጎጂው የሚገባውን ካሳ ለማስላት የተጎጂውን የሥራ ኹኔታ ማወቅ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው የጠቆሙት ከፍተኛ የሕግ ባለሙያው ጉዳት የደረሰበት ሰው ተቀጥሮ የሚሠራ፣ የራሱን ሥራ እየሠራ የሚኖር ወይም ሥራ በመሥራት ላይ ያልነበረ ሰው ሊኾን ይችላል ይላሉ፡፡

ተቀጥሮ የሚሠራ ሰው ላይ ጉዳት ቢደርስ ወደ ካሳው ጉዳይ ከመሄዳችን በፊት በቅድሚያ ጉዳቱ የደረሰው ከሥራው ጋር በተገናኘ መኾን አለመኾኑን መለየት የግድ አስፈላጊ ነው ብለዋል፡፡

ጉዳቱ የደረሰው ከሥራው ጋር የተገናኘ ከኾነ የክርክር ሂደቱም ኾነ የካሳ አሰላል ሥርዓቱ የሚመራው በአሰሪና ሠራተኛ ሕግ መሰረት አሰሪና ሠራተኛ ሕግ ቁጥር 1064/2010 እና አሠሪና ሠራተኛ ሕግ ቁጥር 1156/2011 እንደኾነ አስገንዝበዋል።

ከሥራው ጋር የማይገናኝ ከኾነ ግን ከውል ውጪ ኀላፊነት የሕግ ድንጋጌዎች መሠረት የሚመራ ይኾናል፡፡ የደረሰውጉዳት ጊዜያዊ ከኾነ ሥራ እስከሚጀምር ድረስ ሊያገኝ ይችል የነበረውን ያክል መጠን ሊያገኝ ይገባዋል፡፡

ጉዳቱ ከፊል ቋሚ ከኾነ ደግሞ መሥራት ባላስቻለው መጠን ልክ ይሰላለታል፡፡ ጉዳቱ ቋሚ ኾኖ እስከነአካቴው መሥራት የማያስችለው ከኾነ ደግሞ እስከ ጡረታ ጊዜው ተሰልቶ ይሰጠዋል ብለዋል፡፡

የአካል ጉዳት በደረሰ ጊዜ የወደፊት ጉዳት ካሳ አሰላል ላይ የደረሰውን የጉዳት መጠን ማገናዘብ እንደ ሚገባም ገልጸዋል፡፡ ጉዳቱ በደረሰ ጊዜ የሠራተኛው የገቢ መጠን እና ተጎጂው ጡረታ ለመውጣት የቀረው ጊዜ በሚገባ መጤን ይገባቸዋል፡፡

የራሱን ሥራ እየሠራ ሲተዳደር የነበረ ሰው ጉዳት ቢደርስበት ካሳውን ለማስላት የሚያስችለውን ገቢ ለማወቅ ሊከብድ ይችላል የሚሉት ከፍተኛ የሕግ ባለሙያው ቢኾንም የተለያዩ ዘዴዎችን በመጠቀም ወርሐዊ ወይም የዓመት አማካይ ገቢውን በማየት ያጣውን ወይም ሊያጣ የሚችለውን ጥቅም በማስላት ካሳውን መተመን ይቻላል ነው ያሉት፡፡

በሌላ በኩል በሕመም፣ ለመሥራት ባለመፈለግ፣ የሚመጥነውን ሥራ በማጣት ወይም በጠቅላላው ሥራ አጥ በመኾን ሥራ እየሠሩ ያልነበሩ ሰዎች ላይ ጉዳት ቢደርስባቸው የገቢውን መጠን ማወቅ ስለሚያስቸግር ካሳውን ማስላት ያስቸግራል ብለዋል፡፡ ስለዚህ ዳኞች በርትእ ካሳውን ለማስላት ይገደዳሉ ነው ያሉት፡፡

በአደጋ ምክንያት ሞት ባጋጠመ ጊዜ ካሳ የመጠየቅ መብት ያለው ማነው የሚለው ወሳኝ ጉዳይ ነው የሚሉት ከፍተኛ የሕግ ባለሙያው የፍትሐ ብሔር ሕግ ቁጥር. 2095 መሰረት የሟች ባል ወይም ሚስት፣ የሟች ወላጆች እና የሟች ተወላጆች ካሳ መጠየቅ እንደሚችሉ አስገንዝበዋል።

ለነዚህ ሰዎች የሚከፈለው ካሳ የቀለብ ስለኾነ በቤተሰብ ሕጉ መሠረት ቀለብ ጠያቂ ሊያሟላቸው የሚገቡ መስፈርቶችን ማሟላት እና ማስረዳት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል፡፡

ለህሊና ጉዳት የሚከፈል ካሳ ሌላው የካሳ አይነት ሲኾን ይህም የሰው ልጅ የውስጥ ስሜት ጉዳት ስለኾነ ካሳውን በገንዘብ መለካት በጣም አስቸጋሪ እንደሚኾን ጠቁመዋል፡፡

ኾኖም የህሊና ጉዳት በሚያጋጥም ጊዜ የገንዘብ ካሳ እንደሚከፈል በፍትሐ ብሔር ሕግ ቁጥር 2105(1) ተቀምጧል ነው ያሉት፡፡

የህሊና ጉዳት በልዩ ኹኔታ በሕግ ለተመለከቱ ጉዳቶች እንጂ ሁሌም ካሳ እንደማያስከፍልም የፍትሐ ብሔር ሕግ ቁጥር 2105(2)) ስለመደንገጉ ጠቁመዋል፡፡

የህሊና ጉዳት ካሳ የሚወሰነው ርትእን መሰረት አድርጎ የፍትሐ ብሔር ሕግ ቁጥር 2106-2115 እደኾነም አስገንዝበዋል፡፡

የህሊናጉዳት ካሳ 1ሺህ ብር መብለጥ እንደሌለበት የፍትሐ ብሔር ሕግ ቁጥር 2116(3) እንደሚያስቀምጥ አትተዋል፡፡

ጉዳት መድረሱ፣ ለጉዳቱ ማን ኃላፊነት እንደሚውስድ እና የካሳ ክፍያው መጠን ከተለየ በኋላ መወሰን ያለበት ሌላ ወሳኝ ጉዳይ የካሳ አከፋፈል ሥርዓቱ ነው ይላሉ ከፍተኛ የሕግ ባለሙያው የቁርጥ ክፍያ እና በየጊዜው የሚደርግ ክፍያ ተብለው የሚታወቁ ሁለት አይነት የካሳ አከፋፈል ሥርዓቶች እንደሚኖሩም ነው የተናገሩት፡፡

በቁርጥ ስለሚደረግ ክፍያ ሲባል የካሳ ክፍያ የተወሰነበትን መጠን ያክል በአንድ ጊዜ ለባለመብቱ በመክፈል የሚፈጸም ሲኾን መርሑ እና በብዙ ሀገሮች የሚተገበረውም የአከፋፈል ሥርዓት እንደኾነም ጠቁመዋል፡፡

መርሑ የጉዳት ካሳን በቁርጥ መክፈል ቢኾንም በልዩ ኹኔታ ግን በየጊዜው እንዲከፈል አድርጎ መወሰን እንደሚቻል በሕጉ ተቀምጧል ይላሉ ከፍተኛ የሕግ ባለሙያው፡፡

ነገር ግን ካሳን በየጊዜው እንዲከፈል አድርጎ ለመወሰን መሟላት ካለባቸው ውስጥ የካሳው ባህሪ፣ የአካባቢ ኹኔታዎች እና የካሳ ከፋዩ ማረጋገጫ መስጠት እንዳለበት ነው የጠቆሙት፡፡

በአሰፋ ልጥገበው

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleየሚኒስትሮች ምክር ቤት የ2018 ዓ.ም ሀገራዊ እቅድን ለሁለተኛ ተከታታይ ቀናት እየገመገመ ነው።
Next articleበኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር ከሰላም ማስከበር ጎን ለጎን በርካታ ፕሮጀክቶች ተገንብተዋል።