በአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ከ66 ሺህ በላይ ወጣቶችን የሥራ እድል ተፈጥሮላቸዋል።

11

እንጅባራ: ሐምሌ 05/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ሥራና ሥልጠና መምሪያ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከ66 ሺህ በላይ ወጣቶችን በተለያዩ የሥራ መስኮች ማሰማራ መቻሉን ገልጿል።

መምሪያው የ2017 በጀት ዓመት እቅድ አፈጻጸም ግምገማና የቀጣይ ዓመት እቅድ ትውውቁን ባለ ድርሻ አካላት በተገኙበት በእንጅባራ ከተማ አካሂዷል።

የብሔረሰብ አሥተዳደሩ ሥራና ሥልጠና መምሪያ ኀላፊ ታፈረ ከበደ የተጠናቀቀው በጀት ዓመት ለኢንተርፕራይዞች የተሻለ ድጋፍ የተደረገበት፤ የመረጃ አያያዝ ሥርዓትን ለማዘመን ጥረት የተደረገበት፤ ኮሌጆችን በአዳዲስ መሪዎች ማጠናከር የተቻለበት እና በችግር ውስጥ ኾኖ የመሥራት ባሕል የጎለበተበት እንደነበር ገልጸዋል።

በአንፃሩ ሁሉንም ፀጋዎች አሟጦ አለመጠቀም፣ የዘላቂነት መጓደል፣ የተፈጠረው የሥራ እድል ከሚጠበቀው በታች መኾን እንዲኹም አካል ጉዳተኞችን እና ሴቶችን በበቂ ኹኔታ አለማሳተፍ በበጀት ዓመቱ የነበሩ ድክመቶች ነበሩ ብለዋል።

በብሔረሰብ አሥተዳደሩ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከ70 ሺህ በላይ ለሚኾኑ ወጣቶች የሥራ እድል ለመፍጠር ታቅዶ 66 ሺህ 111 የሚኾኑ ወጣቶችን በተለያዩ የሥራ መስኮች ማሰማራት ተችሏል ብለዋል። የተፈጠረው የሥራ እድል ከእቅዱ አንፃር 90 ነጥብ 3 በመቶ እንደኾነም ገልጸዋል።

በበጀት ዓመቱ ከተፈጠረው የሥራ እድል ውስጥ 2027 የሚኾነው በውጭ ሀገር የሥራ ስምሪት የተፈጠረ የሥራ እድል እንደኾነም አንስተዋል።

የአምራች ኢንንዱስትሪ ዘርፎች፣ የአገልግሎት ዘርፍ፣ የከተማ ግብርና፣ ኮንስትራክሽንና ሌሎችም ለወጣቶቹ የሥራ እድል የፈጠሩ የሥራ መስኮች ናቸውም ብለዋል።

የሥራ እድል ለተፈጠረላቸው ወጣቶች ከ1ሺህ ሄክታር በላይ መሬት፣ 95 ሸዶች እና ከ22 ሚሊዮን ብር በላይ የመሥሪያ ብድር መመቻቸቱንም ገልጸዋል።

የግምገማ መድረኩ ተሳታፊዎችም ለሚፈጠሩ የሥራ ዕድሎች ዘላቂነት ትኩረት ሰጥተው እየሠሩ መኾናቸውን ተናግረዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበሚተካ ደም የማይተካ ሕይወት መታደግ አስደሳች ስጦታ ነው።
Next articleየሚኒስትሮች ምክር ቤት የ2018 ዓ.ም ሀገራዊ እቅድን ለሁለተኛ ተከታታይ ቀናት እየገመገመ ነው።