
ለግብጽ የጦር ሰፈር ግንባታ የተፈቀደ ምንም ዓይነት ቦታ አለመኖሩን ደቡብ ሱዳን ገልጻለች።
ዛሬ በተለያዩ የማኅበራዊ ትሥሥር ገፆችና የዜና ምንጮች ሲዘዋወሩ ከነበሩ መረጃዎች አንዱ ግብጽ በደቡብ ሱዳን ፓጋክ በተባለ ቦታ አካባቢ የጦር “ካምፕ” ለመገንባት ያቀረበችው ጥያቄ አወንታዊ ምላሽ ማግኘቱን የተመለከተው አንዱ ነው።
ጁባ ቲቪ ዘገበው ተብሎ የተሠራጨው መረጃ “ግብጽ በደቡብ ሱዳን ላይኛው የናይል ግዛት ፓጋክ በተባለ ቦታ አቅራቢያ የጦር ሰፈር ለመገንባት ላቀረበችው ጥያቄ ይሁንታ አገኘች” የሚል ነው።
የደቡብ ሱዳን የውጭ ጉዳይና ዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስቴር ዛሬ እንደገለጸው ደግሞ መረጃው ሀሰተኛና መሠረተ ቢስ ነው። በሀገሪቱ ግዛት ውስጥ ለግብጽ የተፈቀደ ምንም መሬት እንደሌለ፣ ይህን በተመለከተ የተደረገ ሥምምነትም አለመኖሩን ነው ሚኒስቴሩ የገለጸው።
ኢትዮጵያ እና ግብጽ በበርካታ ዘርፎች የሚደግፏት ወዳጆቿ መሆናቸውን ያስታወቀው መግለጫው በሀገሪቱ ሰላም እንዲሰፍን ሲያደርጉት የነበረውን ጥረትም አስታውሷል።
በአብዬ ግዛት በተሰማራው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሰላም ማስከበር ጥምር ኃይል ውስጥ ኢትዮጵያ ሰላምን ለማረጋገጥ እያበረከተች ያለውን አስተዋጽዖም ሚኒስቴሩ ጠቅሷል።
የተሳሳተ መረጃውም በሀገሪቱ ሰላም እንዲኖር የማይፈልጉ፣ ደቡብ ሱዳን ከጎረቤቶቿ እና ከቀጣናው ሀገራት ጋር ያላት ሰላም እንዲናጋ የሚሹ ጠላቶች ያሰራጩት እንደሆነ ነው በመግለጫው ያስታወቀው።
ሀገሪቱ ሰላም ፈላጊ መሆናን እና በጋራ ተጠቃሚነት መርህ ላይ በመመሥረት የጎረቤት፣ የአካባቢውና የዓለም ሀገራትን ሰላም እንደምትደግፍም ነው የውጭ ጉዳይና ዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስቴሩ የገለጸው።