
ደሴ፡ ሐምሌ 08/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በደቡብ ወሎ ዞን አሥተዳደር የሥራ ኀላፊዎች እና የመንግሥት ሠራተኞች የክረምት በጎ ፈቃድ የደም ልገሳ መርሐ ግብር ዛሬ አካሂደዋል።
አስተያየታቸውን ለአሚኮ ከሰጡት ሠራተኞች መካከል አቶ ደሳለኝ ንጉሴ ከዚህ ቀደም 13 ጊዜ ደም እንደለገሱ እና በቀጣይም እንደሚለግሱ ተናግረዋል።
ደም መለገስ ደስታን እንደሚያጎናጽፋቸው እና ምንም ችግር እንደሌለውም አስታውሰዋል።
የደቡብ ወሎ ዞን ሴቶች ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ መምሪያ ኀላፊ ቤቴልሔም ብርሃኑ በሚተካ ደማችን የማትተካ እናትን እንዲኹም በተለያየ ችግር ውስጥ ኾነው ደም የሚያስፈልጋቸውን ወገኖች መታደግ መቻል የሁሉም ተግባር መኾን አለበት ብለዋል።
ደማቸውን በየጊዜው እንደሚለግሱ የገለጹት ወይዘሮ ቤቴልሔም “ደም ስንለግስ ደማችን ያልቃል” ብለው የተሳሳተ አመለካከት ያላቸው የማኅበረሰብ ክፍሎች ምንም ችግር እንደሌለው ከልምዳቸው ተነስተው ሀሳባቸውን አጋርተዋል።
በመርሐ ግብሩ ላይ ደም የለገሱት የደቡብ ወሎ ዞን ግብርና መምሪያ ኀላፊ አህመድ ጋሎ በድንገተኛ አደጋ እና በወሊድ ወቅት ከፍተኛ ደም ለሚፈሳቸው ወገኖች ሕይወታቸውን መታደግ የሁልጊዜም ተግባር መኾን ይኖርበታል ብለዋል።
የደቡብ ወሎ ዞን ጤና መምሪያ ምክትል ኀላፊ አብዱ መሐመድ ደም ለለጋሹ ከሚሰጣቸው ጥቅሞች መካከል የልብ ድካምን እና በካንሰር የመጠቃት ዕድልን ይቀንሳል ነው ያሉት።
ኀላፊው ደምን በየጊዜው መለገስ ጤናማ የደም ዝውውር እንዲኖር ማድረግ እና ሌሎች በርካታ ጥቅሞች እንዳሉትም አብራርተዋል።
በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ከሚተገበሩ 17 ተግባራት አንዱ የደም ልገሳ መኾኑን የገለጹት የደቡብ ወሎ ዞን ወጣቶች እና ስፖርት መምሪያ ኀላፊ ጀማል ሞላ በዚህ የበጎ ፈቃድ እንቅስቃሴ ከ1ሺህ 500 በላይ ዩኒት ደም እንደሚሠበሠብ ተናግረዋል።
ዛሬ በንቅናቄ እንደመምሪያ የተጀመረው የደም ልገሳ መርሐ ግብር ወደ ወረዳዎች እና ከተማ አሥተዳደሮች በዕቅድ መውረዱንም አስታውቀዋል።
ደም መለገስ ምንም የሚጎዳው ነገር ባለመኖሩ እና ከስጦታዎች ሁሉ ውዱ ስጦታ በመኾኑ አንዱ የበጎነት መገለጫ በማድረግ ሁሉም ደም እንዲለግስ ጥሪ አቅርበዋል።
ዘጋቢ፡-መሃመድ በቀለ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን